
ፍኖተ ሰላም: መስከረም 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የምዕራብ ጎጃም ዞን ሴቶች፣ ሕፃናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ”ለአረጋውያን ደኅንነት መብቶች መጠበቅ ሁለንተናዊ ኀላፊነታችንን እንወጣ” በሚል መሪ መልዕክት የአረጋውያን ቀን በፍኖተ ሰላም ከተማ አክብሯል።
አረጋውያን የማኅበረሰብ የታሪክ ባለቤቶች መኾናቸውን የምዕራብ ጎጃም ዞን የአረጋውያን ማኅበር ሠብሳቢ በፍቃዱ ዲሳሳ ገልጸዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ መልካም እሴቶች እንዲጎለብቱ እና ለትውልድ እንዲተላለፉ አረጋውያን አበርክቷቸው የጎላ ነው ብለዋል።
አረጋውያን በዕድሜ ምክንያት ብቻ ለችግሮች ተጋላጭ ይሁኑ እንጂ ችግሮች በውይይት፣ በምክክር እና በሽምግልና እንዲፈቱ የማይተካ ሚና ተወጥተዋል ነው ያሉት። በመኾኑም ለሀገር ያበረከቱትን አስተዋጽኦ በማሰብ ማገዝ እና መደገፍ ይገባልም ብለዋል።
በዞኑ አጋዥ የሌላቸው አረጋውያንን ከአጋር አካላት ጋር በመኾን ድጋፍ እየተደረገ መኾኑን የምዕራብ ጎጃም ዞን ሴቶች፣ ሕፃናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ስለእናት ዘሪሁን ተናግረዋል።
አቅም የሌላቸውን አረጋውያንን በቋሚነት ለመደገፍ በፍኖተ ሰላም ከተማ ባለ ስድስት ወለል ሕንፃ ለመገንባት እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
ለዚህም 864 ካሬ ቦታ ርክክብ መደረጉን አንስተው ግንባታውን በዚህ ዓመት ለማስጀመር እየተሠራ ነው ብለዋል።
በፕሮግራሙ አቅም ለሌላቸው አረጋውያን ድጋፍ ተደርጓል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን