ፕሮግራሙ በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ እንዲገባ የመንግሥትን ልዩ ትኩረት ይፈልጋል።

5

ባሕር ዳር: መስከረም 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ከቆቦ እስከ ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ማልማት እንደሚችል እቅድ የተቀመጠለት ፕሮጀክት ነው፤ የቆቦ ጊራና ሸለቆ ልማት ፕሮግራም።

ፕሮግራሙ በከርሰ ምድር እና በገፀ ምድር ውኃ ከ73 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በመስኖ ለማልማት እቅድ የተነደፈለት መኾኑን ነው የፕሮግራም ጽሕፈት ቤት ኀላፈው መንገሻ አሸብር ለአሚኮ የተናገሩት።

የቆቦ ጊራና ሸለቆ ልማት ፕሮግራም በሰሜኑ ጦርነት በደረሰበት ውድመት ምክንያት በእቅዱ ልክ መፈጸም እንዳልቻለ ኀላፊው ተናግረዋል። አሁን ላይ ፕሮግራሙ ራሱን እንደአዲስ አደራጅቶ በ2017 የአካባቢውን አርሶ አደሮች በመስኖ ተጠቃሚ ለማድረግ ሠርቷል ብለዋል።

በዚህም በተጠናቀቀው 2017 ዓመት ፕሮግራሙ በ40 የመስኖ ፕሮጀክቶች 2 ሺህ 830 ሄክታር መሬትን በመስኖ በማልማት የአርሶ አደሮችን የኑሮ ሁኔታ እንዲሻሻል ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል። 43 ሺህ በላይ የቤተሰብ አባላት በልማቱ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ነው ኀላፊው የገለጹት።

በ2018 በጀት ዓመትም በአካባቢው የሚታየውን የዘር ብዜት እጥረትን ለመፍታት የተመረጡ የሰብል አይነቶችን በመለየት እያለማ እንደሚገኝ እና የቆላ ፍራፍሬ ልማት ሽፋንን ለማሳደግ በተመረጡ ችግኝ ጣቢያዎች ችግኞችን ለማልማት ወደ ሥራ መገባቱን ኀላፊው አስረድተዋል።

የቆቦ ጊራና ሸለቆ ልማት ፕሮግራም ጽሕፈት ቤት በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ እንዲገባ ከተፈለገ የአካባቢውን የመልማት አቅም ታሳቢ ያደረገ የኀይል እና የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች በፌደራል እና በክልሉ መንግሥት ትኩረት እንዲሰጣቸው ኀላፊው ጠይቀዋል።

በፕሮግራሙ ተጠቃሚ ከኾኑ አርሶ አደሮች መካከል አርሶ አደር አዲሱ በላይ እና አርሶ አደር ዋሴ ማርየ በመስኖ ልማቱ አትክልትና ፍራፍሬ በስፋት አምርተው ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ እንዳደረገቸው ተናግረዋል።

አርሶ አደሮቹ አክለውም የምግብ ዋስትናቸውን ከማረጋገጥ ባለፈ ከነበራቸው የሳር ቤት ወደ ቆርቆሮ በመቀየር የተመቸ ኑሮ እየኖርን ነው ብለዋል።

ዘጋቢ:- ሰመሀል ፍስሀ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleበዓለም አቀፍ ደረጃ በምጣኔ ሃብት ተስተካካይ ሀገር ለመፍጠር ቁሳዊ እና ሰብዓዊ ካፒታልን ከቴክኖሎጂ ጋር ማቀናጀት ያስፈልጋል።
Next articleአረጋውያን አስታራቂ ናቸው።