
ባሕር ዳር: መስከረም 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ትምህርትን የሰው ልጆች ያለ ምንም ልዩነት ሊጠቀሙት የሚገባ መብት እንደኾነ ይነገራል።
የሰው ልጅ ትምህርት የማግኘት መብቱ በአግባቡ ካልተከበረ ሌሎች የሰብዓዊ መብቶች እንዲጣሱም ምክንያት እንደሚኾን ይገለጻል። ሰዎችም ለትምህርት ብለው ከአካባቢያቸው ርቀው መጓዝ ሳያስፈልጋቸው በቀላሉ በአካባቢያቸው እንዲያገኙ መደረግ አለበት።
በአማራ ክልል ያለውን የመማር ማስተማር ሥራ ስንቃኝ ሰናይ እና እኩይ ተግባራትን እናገኛለን። አንዱ ትምህርት እንዳይስተጓጎል ሲጥር፤ ሌላው ደግሞ ትምህርት ቤቶች ተዘግተው ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ እንዲውሉ ሲፍልግ እንመለከታለን።
ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ክልሉ በገጠመው የጸጥታ ችግር ምክንያት ከ4 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ርቀዋል።
በክልሉ በተያዘው የትምህርት ዘመን 7 ነጥብ 4 ሚሊዮን ተማሪዎችን ለማስተማር አቅዶ ወደ ሥራ መግባቱ ይታወሳል። ይሁንና ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ ባለመከፈታቸው በዚህ ዓመት ለማስተማር የታቀደውን ቁጥር እስካሁን ማሳካት አልተቻለም። ይህን መሠረታዊ ነገር የማስተካከል ኀላፊነት ደግሞ የሁሉም ነው።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባዔ ጌትነት እውነቱ (ዶ.ር) የትምህርት ጉዳይ የማይመለከተው የኀብረተሰብ ክፍል የለም ብለዋል። አንድ ሀገር በሁለንተናዊ ዘርፍ እንድታድግ የግድ ዜጎቿ መማር አለባቸው ነው ያሉት።
በትምህርት ያልበለጸገ ዜጋ ያለበት ሀገር ሁልጊዜ በድኀነት አዙሪት ይኖራል እንጅ ስኬት ላይ አይደርስም ብለዋል። ከሌሎች ሀገራት ጋርም ተወዳዳሪ መኾን እንደማይችል ነው የተናገሩት።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ምክር ቤትም “በትምህርት ጉዳይ የማይመለከተው ዜጋ እና ተቋም የለም”በሚል እሳቤ በየጊዜው ሕዝብ የሚወያይበትን መድረክ በማዘጋጀት የተቋረጠው ትምህርት እንዲቀጥል ኀላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የሃይማኖት አባቶችን ሃሳብ የማይቀበል የኀብረተሰብ ክፍል ባለመኖሩ በእነርሱ በኩል ስለትምህርት ግንዛቤ የማስረጽ ሥራ መከናወኑንም ተናግረዋል።
በየቀበሌውም የሀገር ሽማግሌዎች ጋር በመወያየት ትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱ እና ወላጆችም ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት እንዲልኩ ኀላፊነታቸውን መወጣታቸውን ጠቁመዋል።
እንደ ባሕር ዳር ከተማ ምክር ቤት የማኀበረሰብ አንቂዎችን በመጠቀምም መማር ማስተማሩን ለመደገፍ መሠራቱን ተናግረዋል።
በየደረጃው የሚገኙ የቀበሌ፣ የከተማ እና የክልል የሕዝብ ወኪሎች ትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱ እና ወላጆችም ልጆችን እንዲልኩ በየመድረኩ አግባብተዋል ነው ያሉት። በተሠራው ሥራ እንደከተማ አሥተዳደር አወንታዊ ውጤት ተገኝቷል ነው ያሉት።
በአንዳንድ አካባቢዎች ትምህርት ቤቶች ራቅ ያለ ቦታ ስለሚገኙ ኀብረተሰቡ መምህራንን አይዟችሁ በማለት መሠረተ ልማቱን እንደራሱ ሃብት እንዲጠብቅ የምክር ቤት አባላት ሕዝባዊ አደራቸውን እየተወጡ ይገኛሉ ብለዋል። እገዛ እና ድጋፋችንም ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
የመማር ማስተማር ሥራ ለነገ ይደር የማይባል የአንዲት ሀገር የዕለት ከዕለት ዐበይት ተግባር ነው ያሉት አፈጉባኤው ሁሉም የኀብረተሰብ ክፍል ሂደቱን በየቀኑ እየተከታተለ መደገፍ ይኖርበታል ብለዋል።
ነገ ላይ መልካም አሥተዳድርን የሚሻ፣ ጥሩ ሕክምናን የሚፈልግ፣ እድገት እና ብልጽግናን የሻተ፣ ሀገሩ ከሌሎች ያደጉ ሀገራት ተርታ እንድትሰለፍ ቀናኢ ፍላጎት ያለው የኀብረተሰብ ክፍል የግድ ዛሬ ልጆቹን ማስተማር አለበት ነው ያሉት። “የድህነት እና የኋላቀርነት ማምከኛ ብልሃቱ የተማረ ዜጋ ሲፈጠር ብቻ ነው “ብለዋል።
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር የምክር ቤት አባል እሙዬ በቀለ ከላይ እስከ ታች የሚገኙ የምክር ቤት አባላት እንደ ክልል የገጠመውን የትምህርት ስብራት ለመጠገን ሠርተናል፤ እየሠራንም እንገኛለን ብለዋል።
ተናበው በመሥራታቸውም ትምህርት ቤቶች ተከፍተው መማር ማስተማሩ ከባለፈው ዓመት በተሻለ መልኩ እየተከናወነ ይገኛል ነው ያሉት።
ዛሬ ያልተማረ ዜጋ ነገ ሀገር መረከብ አይችልም የሚሉት የምክር ቤት አባሏ አሁንም ወላጅ ትምህርት ቤት ያልመጣ ልጅ ካለው የመላክ ሀገራዊ ግዴታ እና ኀላፊነት እንዳለበት ተናግረዋል።
እንደራሴዎች የሕዝብ ወኪሎች ናቸው፤ በየጊዜው የሕዝብ መድረክ በመፍጠር እና የተጠናከረ የሕዝብ ግንኙነት ሥራ በማከናወን አንድም ተማሪ ከትምህርት ውጭ እንዳይውል እና መማር ማስተማሩ ለአፍታም ቢኾን እንዳይቋረጥ ሕዝባዊ አደራችንን መወጣት ይገባቸዋል ነው ያሉት።
ዘጋቢ:- ሙሉጌታ ሙጨ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!