
ሁመራ: መስከረም 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሰቲት ሁመራ አንደኛ ደረጃ መናኻሪያ ዲጂታል የትኬት
አገልግሎቱን መስጠት ጀምሯል።
ዲጂታል የትኬት አገልግሎት በመናኻሪያዎች ተግባራዊ መደረጉ ለተሳፋሪዎች እና ለአሽከርካሪዎች እንግልትን በመቀነስ የትራፊክ እንቅስቃሴውን ጤናማ ማድረግ እንደሚያስችል የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ገልጿል።
በመናኻሪያዎች አካባቢ የሚያጋጥሙ የታሪፍ ጭማሪ፣ እንግልት፣ ከመጠን በላይ መጫንን ለማስቀረት የዲጂታል ትኬቱ ሚና ከፍተኛ መኾኑን ተሳፋሪዎች እና አሽከርካሪዎች ለአሚኮ ተናግረዋል።
የነዳጅ እጥረት ከፍተኛ ችግር መኾኑን አሽከርካሪዎች አንስተዋል። በእጥረቱ ሰበብ በከፍተኛ ዋጋ ነዳጅ እንደሚገዙ የሚያስረዱት አሽከርካሪዎቹ ይሄም መመሪያው ላይ ከተቀመጠው ታሪፍ ጋር የማይመጣጠን በመኾኑ ለሥራ ጫና እንደፈጠረባቸው አንስተዋል።
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ለምለሙ ባየህ
የዲጂታል ትኬት አገልግሎት መጀመሩ ለአገልግሎት ሰጭውም ኾነ ለአገልግሎት ፈላጊው ወጭን እና እንግልትን ይቀንሳል ብለዋል።
አገልግሎቱ በትርፍ እና በታሪፍ ቁጥጥር ሥራው ላይ አመች ኹኔታዎችን አንደሚፈጥርም ጠቁመዋል።
ከነዳጅ ዋጋ ጋር የታሪፍ አለመጣጣምን በተመለከተ አሽከርካሪዎች የሚያነሱትን ጥያቄ ለመመለስ እየተሠራ ነው ብለዋል። ከመፍትሔ ርምጃዎቹ መካከል የሚቀርበውን ነዳጅ አግባብ ያለው ስርጭት እንዲኖረው ማድረግ መኾኑንም አንስተዋል።
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ገብረእግዚአብሔር ደሴ
የመናኻሪያ አገልግሎት የኅብረተሰቡ የመልካም አሥተዳደር እርካታ ከሚለካባቸው አገልግሎቶች መካከል አንዱ መኾኑን ገልጸዋል።
የዲጂታል ትኬትን መጠቀም መቻል ከታሪፍ እና ከልክ በላይ መጫንን በማስቀረት ለኅብረተሰቡ ተመጣጣኝ አገልግሎት መስጠት እንደሚያስችል ተናግረዋል።
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና የሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ የዲጂታል ትኬት አገልግሎትን በመናኻሪያዎች ተግባራዊ ማድረግ የአገልግሎት አሰጣጡን ቀልጣፋ እንደሚያደርገው ገልጸዋል።
ይሄም ወጭን እና እንግልትን በመቀነስ የትራፊክ እንቅስቃሴውን ጤናማ ለማድረግ ያግዛል ብለዋል።
ኅብረተሰቡም ስለአገልግሎቱ ጠቀሜታ በመረዳት መብቱን በአግባቡ መጠቀም እንዳለበት አስገንዝበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!