
ባሕር ዳር: መስከረም 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመኾን የጎደና ላይ ልጆችን በማንሳት ወደ ቤተሰቦቻቸው የመቀላቀል እና ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ እያደረገ ነው።
መኳንንት ክፍሉ የ10ኛ ክፍል ተማሪ ነው። ወላጆቹ በሕይወት ባለመኖራቸው ምክንያት ከአያቶቹ ጋር በመኾን ይማር እንደነበር ተናግሯል። ከጊዜ በኋላም አስተማሪ አያቶቼን በሞት አጣሁ የሚለው መኳንንት አማራጭ ፍለጋ ወደ ከተማ በመሄድ ከአጎቴ ጋር በመኾን ትምህርቴን ቀጥየ ነበር ብሎናል።
በዚያም እየተማረ እያለ በግጭቱ ምክንያት ትምህርት በመዘጋቱ ወደ ባሕር ዳር ከተማ በመምጣት የጎዳና ላይ ሕይወትን እንደጀመረ ነው የተናገረው።
የጎዳና ተዳዳሪ መኾን ከጀመርኩ አንድ ዓመት ተኩል ኾኖኛል ያለው መኳንንት የጎዳና ሕይወት ከርሃቡ፣ ከጥሙ፣ ከፀሐዩ እና ከቁሩ ባለፈ መልካም ላልኾኑ ስብዕናዎች የመጋለጥ ዕድልን ያሰፋል ብሎናል። ሱስ ካለባቸው ልጆች ጋር መዋሉም በጣም አስቸጋሪ እንደኾነ ነው የገለጸው።
እስካሁን ባለው ሁኔታ ምንም አይነት የሱስ ተጠቂ አይደለሁም የሚለው መኳንንት የአቻ ግፊቱ እና የምውልበት ቦታ በራሱ ወደ ሱስ እንድገባ ተጽዕኖ የሚያሳድር ነው ብሏል።
ጎዳና ላይ በመዋሌ በጣም አዝኘ ነበር ያለን ተማሪ መኳንንት የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ከአጋር ድርጅቱ ጋር በመኾን ሙሉ ወጭየን በመሸፈን “ያቋረጥኩትን ትምህርት እንድጀምር ዕድል ስለሰጠኝ እንደገና የመወለድ ያህል ተሰምቶኛል ነው” ያለው።
በፊትም ጎበዝ ተማሪ ነበርኩ ያለን መኳንንት የተሰጠኝን ዕድል በደንብ ተጠቅሜ እና ጠንክሬ ተምሬ ውጤታማ ለመኾን የመጨረሻ አቅሜን እጠቀማለሁ ብሏል።
አምላኩ ማረው ደግሞ የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ነው። ከአንድ እስከ 10 ባለው ደረጃ የሚወጣ ጎበዝ ተማሪ እንደነበር ነግሮናል።
በግጭቱ ምክንያት ትምህርት በመዘጋቱ እና ቤተሰቦቹ የአቅም ውስንነት ስላለባቸው እራሱን ለመርዳት ሲል ወደ ባሕር ዳር ከተማ በመምጣት የጎዳና ተዳዳሪ እንደኾነ ነው የነገረን።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ከአጋር ድርጅት ጋር በመኾን ከጎዳና ላይ በማንሳት እና የሚያስፈልገውን የትምህርት ቁሳቁስ በማሟላት ወደ ቤተሰቦቹ እንዲመለስ እና ትምህርቱን እንዲጀምር ምቹ ሁኔታ ስለፈጠለት መደሰቱን ገልጿል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ሰብለ ዘውዱ
በተፈጥሯዊም ሆነ ተፈጥሯዊ ባልኾነ ምክንያት ችግር የገጠማቸው ቁጥራቸው በርካታ የኾኑ ልጆች ከአካባቢያቸው በመፈናቀል ወደከተማዋ እንደሚመጡ ተናግረዋል።
እነዚህን ልጆች የማበረታታት እና ከተለያዩ ጉዳቶች የመጠበቅ ግዴታ አለብን ያሉት ኀላፊዋ ልጆች ከቤተሰቦቻቸው ተፈናቅለው ወደ ጎዳና እንዳይወጡ፣ ከትምህርታቸው እንዳይፈናቀሉ እና የጉዳት ሰለባዎች እንዳይኾኑ በየዞን እና በየወረዳው ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል።
ነገር ግን አሁንም ከየአካባቢው እየተፈናቀሉ የሚመጡ ልጆችን ማስቆም እንዳልተቻለ አንስተዋል።
ከቤተሰቦቻቸው ተፈናቅለው የመጡ ልጆችን ወደ ቤተሰቦቻቸው በመቀላቀል እንዴት ወደ ትምህርት ገበታቸው እንመልሳቸው በማለት ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመኾን ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲመለሱ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ መኾኑን ገልጸዋል።
በመጀመሪያ ልጆች አሁን ላይ ካሉበት እሳቤ፣ ድብርት እና ከተለያዩ ሱሶች እንዲወጡ ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመኾን በባለሙያዎች የሥነ ልቦና እገዛ እንደሚደረግላቸው ገልጸዋል።
በቀጣይም ማንኛውም የኅብረተሰብ ክፍል ይህንን በጎ ተግባር እንደ አርዓያ በመውሰድ በሚችለው አቅም ሁሉ በመደገፍ የበኩሉን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
ዘጋቢ:- ሰናይት በየነ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!