የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ወደ ፐብሊክ ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ለውጥ አደረገ።

3

አዲስ አበባ፡ መስከረም 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ (Ethiopian Civil Service University) ለዘጠኝ ወራት ሲያካሂደው የነበረውን የሪፎርም ጥናት በማጠናቀቅ ስሙን ወደ የኢትዮጵያ ፐብሊክ ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ (Ethiopian Public Service University – EPSU) መቀየሩን ይፋ አድርጓል።

ከሦሥት አሥርት ዓመታት በላይ ያስቆጠረው ዩኒቨርሲቲው በትምህርት ሚኒሥቴር፣ በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን እና በራሱ ባለሙያዎች የተካሄደውን ጥናት መሠረት በማድረግ፣ ለዘመናዊ የመንግሥት አሥተዳደር የሚያስፈልገውን ዕውቀት እና ክህሎት የታጠቀ የሰው ኃይል በብቃት ለማፍራት የሚያስችል አዲስ አደረጃጀት እና የለውጥ መስመር መዘርጋቱን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ንጉስ ታደሰ (ዶ.ር) አስታውቀዋል።

ዩኒቨርሲቲው ከዚህ ቀደም የመንግሥት ሠራተኞችን ብቻ ይቀበል ከነበረበት አሠራር በመውጣት የ12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ እና የመግቢያ ውጤት ያመጡ ተማሪዎችን እንዲኹም ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎችን በዝውውር ለመቀበል የሚያስችል ሥርዓት ዘርግቷል ነው ያሉት።

ሪፎርሙ ዩኒቨርሲቲው በመንግሥት የልማት ሥራዎች ተጨማሪ አቅም የሚፈጥሩ የሲቪል ሰርቪስ መሪዎች እና ባለሙያዎችን በማፍራት ላይ ትኩረት እንዲሰጥም ያስችላል ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው ትልቅ የልህቀት ተቋም እንዲኾን ከፍተኛ ዝግጅት መደረጉን እና ለዚህም የአሠራርና የመሰረተ-ልማት ዝግጅት መደረጉን ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል።

ዶክተር ንጉስ ታደሰ እንዳሉት ይህ ለውጥ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን በመላ ሀገሪቱ ከሚተገብረው የሪፎርም ሥራ ጋር የተጣጣመ ሲኾን፣ ዩኒቨርሲቲውን እንደ አዲስ ለማደራጀት ያለመ ነው።

ለውጡ በአጭርና በረዥም ጊዜ የሚከናወኑ ምዕራፎች እንዳሉትም ተጠቅሷል።

ዘጋቢ፦ ሰለሞን አሰፌ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በሰላም እጦት ምክንያት ከቤተሰቦቼ ርቄ ለመማር ተገድጃለሁ” ከቤተሰቦቿ ርቃ የምትማር ተማሪ
Next article“ዳግም ትምህርቴን እንድማር ዕድሉ ስለተሰጠኝ እንደገና የመወለድን ያህል ቆጥሬዋለሁ” ትምህርት አቋርጦ የነበረ ተማሪ