“በሰላም እጦት ምክንያት ከቤተሰቦቼ ርቄ ለመማር ተገድጃለሁ” ከቤተሰቦቿ ርቃ የምትማር ተማሪ

7

ባሕር ዳር፡ መስከረም 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ባለፉት ዓመታት በአማራ ክልል የተከሰተው ግጭት በተማሪዎች ሕይዎት ላይ ተጽዕኖ ማሳረፉን ተማሪዎች ተናግረዋል።

ተማሪዎቹ የሰላም መስፈን ጥቅሙ የጋራ ነው፤ ሰላም ማጣታችንም ጉዳቱ ለሁላችንም ነው ብለዋል። ሰላም እንዳይደፈርስ ካለፈው መማር ይገባል የሚሉት ተማሪዎቹ የሰላም ዋጋ ከሚገለጸው በላይ እንደኾነም አስረድተዋል።

ባለፉት ዓመታት በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተከስቶ የቆዬው ግጭት ተማሪዎችን ለከፋ ፈተና ዳርጎ ቆይቷል።

በሰላም እጦት ምክንያት ከቦታቸው ተፈናቅለው ትምህርታቸውን ለመከታተል የተገደዱ በርካታ ተማሪዎች አሉ።

የ9ኛ ክፍል ተማሪ የኾነችው ትርንጎ ይልማ ከወላጆቿ እና ዘመዶቿ ጋር ትምህርቷን ስትከታተል መቆየቷን ለአሚኮ ትናገራለች።

ይሁን እንጂ በአካባቢው የትምህርት ሂደቱን ለመከታተል የሚያስችል ምቹ ሁኔታ በመጥፋቱ ምክንያት ትምህርቷን ለመቀጠል ተቸግራ መቆየቷን አንስታለች።

“የሰላሙ ሁኔታ በትምህርቴ ላይ ጫና ያሳድርብኛል ብዬ ስለፈራሁ፣ አንድ ጊዜ ሲዘጋ አንድ ጊዜ ሲከፈት፣ ተቋርጦም ሊቀር ይችላል በሚል ስጋት ወደ ኋላ መቅረት አልፈልግም ብዬ ከቤተሶቤቼ ርቄ ለመማር ተገድጃለሁ” ነው ያለችው።

ከቤተሰቦቿ ርቃ መማሯ ችግር እንደፈጠረባት እና ብቸኝነት ትልቅ ፈተና እንደኾነባት ገልጻለች።

“ስንቅ ስጨርስ እንኳን ወደ ቤተሰብ ሄጄ ማምጣት የምሳቀቅበት ደረጃ ላይ ደርሻለሁ፤ እንደፈለኩ ቤተሰቦቼን እንኳን ማግኘት አልቻልኩም” ነው ያለችው።

ተማሪዋ ከቤተሰቦቿ ርቃ ስትኖር ለተለያዩ ወጭዎች መዳረጓን ገልጻለች። ከቤተሰቦቿ ጋር ኾና ብትማር ኖሮ ወጭዎቹን መቀነስ ትችል እንደነበር ተናግራለች።

ግጭቱ ሕይወት እየቀጠፈ፣ አካል እያጎደለ እና ንብረት እያወደመ መኾኑን አንስታለች።

“አሁን ላይ ችግሮች እና ግጭቶች ይበቁናል፤ ተማሪዎች መማር፣ ገበሬው የግብርና ሥራውን፣ ነጋዴውም ንግዱን ማሳለጥ እና ሀገርንም በዕውቀት ከፍ ማድረግ ይገባናል፤ እኛም ተማሪዎች በሰላም ተምረን ሀገር የምንጠቅም መኾን ይገባናል” ነው ያለችው።

ሌላኛዋ በጉዳዩ ላይ ለአሚኮ ሃሳቧን ያጋራችው ተማሪ አበበች ሀብታሙ በግጭት ምክንያት ከቤተሰቦቿ ርቃ ትምህርቷን እየተከታተለች መኾኗን ተናግራለች።

ሰላም ማጣት ከግለሰብ ጀምሮ ትልቅ ደረጃ ላይ ያሉ ግለሰቦችን እንደሚጎዳ የገለጸችው ተማሪዋ ከአካባቢያቸው ለቀው ወደ ሌላ ከተማ ሲመጡ ብዙ ችግሮች እንደሚገጥሟቸው ገልጻለች።

“ለቤተሰቦቻችን ማገዝ፣ ማገልገል፣ ከጎናቸው መኾን ሲገባን በተቃራኒው ኾኖ መረዳዳት ያለብንን በጊዜው ሳንረዳዳ ችግሮችን፣ ሀዘኖችን፣ ደስታውንም ቢኾን ሳንካፈል እንቀራለን” ነው ያለችው። የሰላም እጦት በቤተሰብ እና በማኅበረሰብ ትስስር ላይ ስብራት እንደሚፈጥርም ተናግራለች።

ሁሉም ተማሪዎች መማር እንዳለባቸው እና የሚፈለጉት ደረጃ ላይ መድረስ እንዳለባቸው ገልጻለች።

ተማሪ አበበች “እኔ ቤተሰቦቼ የማስተማር አቅም ስላላቸው ተማርኩ፤ ነገር ግን ረዳት የሌላቸው፣ ከቤተሰብ ጋር ብቻ ኾነው በአቅም ማነስ ምክንያት የሚቀሩ ተማሪዎችን ማሰብ ግድ ይላል” ነው ያለችው።

የሰላም እጦት በትምህርት ዕድል ተጠቃሚነት ላይ የሚፈጥረው ችግር ከፍተኛ መኾኑንም ተናግራለች።

ዘጋቢ፦ ሰማሀል ፍስሀ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአማራ ክልል ፍርድ ቤቶች የዳኞች ጉባኤ እንደቀጠለ ነው።
Next articleየኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ወደ ፐብሊክ ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ለውጥ አደረገ።