
ባሕር ዳር: መስከረም 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ በ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ውጤት ዙሪያ ውይይት እያካሄደ ነው።
በውይይት መድረኩ በከተማ አሥተዳደሩ ትምህርት ቤቶች የሚገኙ ርእሳነ መምህራን፣ ሱፐርቫይዘሮች እና የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ተገኝተዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ሙሉዓለም አቤ (ዶ.ር) የትምህርት ውጤታማነት የሚለካው ደረጃቸውን ጠብቀው በሚሰጡት ብሔራዊ ፈተናዎች ነው ብለዋል። በብሔራዊ ፈተናዎች የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የበርካታ ባለድርሻ አካላትን ርብርብ የሚጠይቅ መኾኑን አንስተዋል።
ባለፈው ዓመት ችግሮችን በመቋቋም ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንዲያመጡ የከተማ አሥተዳደሩ በሥነ ልቦና እና በእውቀት የማዘጋጀት ሥራ መሠራቱን ጠቁመዋል።
ከኩረጃ ነጻ የኾነ የፈተና ሥርዓትን መተግበር የነገ ትውልድን ለማፍራት ዛሬ ላይ እየተተገበረ ያለ አንዱ ተግባር ስለመኾኑም ነው ያነሱት።
በከተማ አሥተዳደሩ የቤተ መጽሐፍትን፣ የቤተ ሙከራ እና ሌሎች የመማር ማስተማር ግብዓቶችን በማሟላት እየተሠራ መኾኑን ነው የገለጹት። መምሪያው ከአጋር እና ባለድርሻ አካላት ጋርም ቅንጅታዊ አሠራርን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አንስተዋል።
የትምህርትን አጀንዳ የግል ኮሌጆች እና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አጀንዳቸው አድርገው ማገዝ እንደሚገባቸው ጠቁመዋል።
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሳይኮሎጅ መምህር የኾኑት እና ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት አውግቸው ሽመላሽ የተማሪዎች ውጤትን ለማሻሻል ችግሩን በሚገባ መለየት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲዎች ከማኅበረሰብ አቀፍ አገልግሎት አንጻር ተማሪዎችን በሥነ ልቦና ግንባት እና የመምህራንን አቅም በመገንባት በኩል ሚናቸው የጎላ መኾኑን አንስተዋል።
የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል ከተማሪዎች እንደሚጀምርም አንስተዋል። ወሳኝ ከኾኑ ጉዳዮች መካከልም የመማር ቁርጠኝነት፣ ለፈተና ያላቸው ዝግጁነት፣ የማንበብ ልምድ ለአብነት አንስተዋል።
ወላጆች፣ መምህራን እንዲሁም በየደረጃው ያሉት የትምህርት ተቋማት የመፈጸም እና የማስፈጸም ኀላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አመላክተዋል።
የብሉ ማርክ ኮሌጅ ዲን አዝመራው አበባው የተማሪዎች የማለፍ ምጣኔ እንዲሻሻል የግል ኮሌጆች የበኩላቸውን መወጣት እንደሚገባቸው አንስተዋል።
ኮሌጁ ኀላፊነቱን ወስዶ በመንስዔዎች፣ ተግዳሮቶች እና መፍትሔዎችን ለማመላከት የሚያስችል ውይይት ማዘጋጀቱን አመላክተዋል። ሌሎች ባለድርሻ አካላትም የራሳቸው አጀንዳ አድርገው ሊሠሩበት እንደሚገባ አንስተዋል።
የውይይት መድረኩ የከተማ አሥተዳደሩ ትምህርት መምሪያ ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ እና ከብሉ ማርክ ኮሌጅ ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ስለመኾኑ ተገልጿል።
ዘጋቢ፦አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን