ተቋማዊ እና ሕጋዊ አሠራሮች ሲጠናከሩ ሕዝብ እና መንግሥትን የበለጠ ያስተሳስራሉ።

2

ባሕር ዳር: መስከረም 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የከተማ ልማት ዘርፍ በተቋማት የማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ እና የሕግ ማዕቀፍ ላይ ውይይት አድርጓል።

ውይይት የተደረገው በአማራ ክልል የመንግሥት ኮንስትራክሽን ባለሥልጣን፣ በአማራ ክልል የመንግሥት ፕላን ኢንስቲትዩት እና በአማራ ክልል የሙያ ብቃት ምዘና እና ማረጋገጫ ባለሥልጣን ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ ነው። የመንግሥት ፕሮጀክቶች አሥተዳደር እና አመራር ሥርዓትን ለመደንገግ በተዘጋጀ ረቂቅ አዋጅ ላይም ውይይት ተደርጓል።

በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አሥተባባሪ እና የከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር) የሕግ ማዕቀፎቹ ከዚህ በፊት በተለያዩ ደረጃዎች ውይይት እንደተደረገባቸው ጠቅሰዋል።

ክልሉ የ25 ዓመታት የአሻጋሪ እድገት እና የዘላቂ ልማት ዕቅድ ማቀዱን የጠቀሱት ኀላፊው ለየዘርፉ የማስፈጸሚያ ስልቶች እንደሚያስፈልጉት አንስተዋል። ከስልቶቹም ውስጥ አንዱ ዕቅዱን ሊሸከሙ የሚችሉ የተቋማት አደረጃጀት እና ሚና መገንባት መኾኑንም ገልጸዋል።

ለጠንካራ ተቋም ጠንካራ የሰው ኀይል፣ የአሠራር ሥርዓት እና ዘመናዊ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ወሳኝ ነው ብለዋል። ጠንካራ ተቋም ካልተገነባ የሀገር ሕልውና አደጋ ላይ ይወድቃል ነው ያሉት።

ተቋማትን ከግለሰቦች ፍላጎት ይልቅ የሀገርን ልማት አስቀድመው የ25 ዓመታት ዕቅዱን ማስፈጸም የሚችሉ አድርጎ መገንባት ይጠበቃል ብለዋል። ለዚህም የሕግ ማዕቀፎችን በአግባቡ አይቶ ማቋቋም እና መገንባት አስፈላጊ መኾኑን ገልጸዋል።

ተቋማዊ እና ሕጋዊ አሠራሮች ሲጠናከሩ ሕዝብ እና መንግሥትን የበለጠ ያስተሳስራሉ ብለዋል። የከተማ ልማት፣ የኮንስትራክሽን፣ የሙያ ብቃት ምዘና ዘርፍ እና የፕሮጀክቶች አሥተዳደር አዋጅ አደረጃጀት እና አሠራራቸው ላይ በመወያየት አዳብሮ የሕግ ማዕቀፍ ማውጣት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።

በጠንካራ ተቋም ግንባታ የታሰበውን ዓላማ ለማሳካት የሚችሉ ዕቅዶች መኖራቸውን ማረጋገጥ አስፈላጊ መኾኑንም አመላክተዋል።

የአማራ ክልል ከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ምክትል ኀላፊ አሰፋ ሲሳይ በክልሉ የ25 ዓመታት የአሻጋሪ እድገት እና የዘላቂ ልማት ዕቅድ መሠረት በአዲስ ከሚቋቋሙት ተቋማት መካከል የኮንስትራክሽን ባለሥልጣን አንዱ መኾኑን ጠቅሰዋል።

በተበታተነ መልኩ ሲመራ የነበረውን ዘርፍ ሠብሠብ በማድረግ በጋራ አመራር ግልጽ እና ፍትሐዊ አሠራርን ማስፈን ማስፈለጉን ገልጸዋል።

ለጥቅል ክልላዊ እድገት ያለውን ሚና ማሳደግ ሌላኛው ዓላማ መኾኑንም አንስተዋል። ኮንስትራክሸኑ በግብርናው እና በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ድርሻውን እንዲወጣም ለማስቻል መቋቋሙን ገልጸዋል።

የኮንስትራክሽን ዘርፉ በታቀደለት ጊዜ እና ዋጋ የመጠናቀቅ ችግርን ለመቅረፍ ያስችላል ነው ያሉት።

ለተቋራጭ እና አማካሪዎች ድጋፍ በመስጠት ከግለሰብ ተቋም ወደ ኮርፖሬት ተቋም ያደጉ ተወዳዳሪ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪዎችን ለመፍጠር እንደሚያስችልም ገልጸዋል። በአንድ ተቋም ክትትል እና ቁጥጥር መደረጉም በዘርፉ የነበረውን ብልሹ አሠራር ለመቆጣጠር ያስችላል ነው ያሉት።

የአማራ ክልል ፕላን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጥላሁን በሪሁን ከተሜነት በሂደት እየተስፋፋ የሚሄድ የኑሮ ዘይቤ መኾኑን ጠቅሰዋል። ከተሞችን በፕላን ማልማት የሚያስችል የተቋም አደረጃጀት አስፈላጊ መኾኑን ተናግረዋል።

ኢንስቲትዩቱ በአዲስ መደራጀቱ ተግባር እና ኀላፊነቱ በግልጽ ተቀምጦ ጥራትን ለማስጠበቅ፣ ተጠያቂነትን ለማስፈን እና የከተሞችን ልማት ለማረጋገጥ እንደሚያስችል ነው የጠቆሙት።

የቀድሞው አሠራር የፕላን ዝግጅት ውስንነት የነበረበት፣ የከተማ ፕላን የሚጣስበት እና የከተሞችን እድገት የማሳለጥ ውስንነት ነበረበት ነው ያሉት። በአዲስ የሚቋቋመው ተቋም አደረጃጀት እና አሠራር እነዚህን ችግሮች የሚፈታ ነው ብለዋል።

ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article39 ሺህ የውጭ ዜጎች በሕገ-ወጥ ሰነድ ሲገለገሉ ተያዙ።
Next articleትምህርትን ሁሉም አጀንዳ ሊያደርገው ይገባል።