
አዲስ አበባ፡ መስከረም 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ባለፈው አንድ ዓመት 39 ሺህ የውጭ ዜጎች በሕገ-ወጥ ሰነድ ሲገለገሉ መያዙን የኢሚግሬሽን እና ዜግነት ጉዳዮች ገልጿል።
እነዚህ ግለሰቦች በኢኮኖሚ አሻጥር ውስጥ ሲሳተፉ የተገኙ ናቸው ብሏል።
የአንድ ሉዓላዊ ሀገር መንግሥት በግዛቱ ውስጥ የሚኖሩ ማንኛውንም ዜጋ የመቆጣጠር የማሥተዳደር እና ሕጋዊነትን የማስያዝ ኀላፊነት አለበት ብለዋል ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ጎሳ ደምሴ።
በኢትዮጵያም ይህን ሥራ የሚያከናውነው የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ተቋም ነው ብለዋል።
ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ወደ ሀገር የገባ ማንኛውም ዜጋ ሕጋዊ ቪዛ እና የመኖሪያ ፈቃድ እንዲኖረው ይገደዳልም ነው ያሉት።
አቶ ጎሳ ደምሴ ሕጋዊ ሰነድ ሳይኖራቸው የሚንቀሳቀሱ የውጭ ዜጎች በአንድ ሀገር ኢኮኖሚ፣ ጸጥታ እና ማኅበራዊ እንቅስቃሴ ላይ ጉዳት እንደሚያደርሱም አብራርተዋል።
ይህንን ለመከላከልም ባለፈው 2017 በጀት ዓመት ብቻ 39 ሺህ ሰነድ አልባ የውጭ ዜጎችን መያዝ ተችሏል ነው ያሉት።
የተያዙት ሰነድ አልባ ሰዎችም በኢኮኖሚ ላይ አሻጥርን የሚያከናውኑ፣ ሕገ ወጥ ማኅበራዊ ክንውን ላይ የተሰማሩ እና የኢትዮጵያን ደኅንነት በሚጎዱ ተግባራት ላይ የተሰማሩ ናቸው ብለዋል።
አግባብነት የሌላቸው ሰነድ የሚጠቀሙበት ምክንያት የተለያዩ ፍላጎቶችን ለማሳካት እንደኾነም አስረድተዋል።
እነዚህ ፍላጎቶች ኢኮኖሚያዊ ጥቅምን ለማሳካት፣ ፖለቲካዊ ፍላጎቶችን ከግብ ለማድረስ፣ የሚሠሩት ሥራ እና እንቅስቃሴያቸው እንዳይታወቅ ከመፈለግ የመጣ እንደኾነም ጠቁመዋል።
እነዚህ ጉዳቶች ያለሰነድ እና ፍቃድ ሲከናወኑ ደግሞ በሀገሪቱ ላይ ጉዳት የሚያስከትሉ በመኾኑ ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ ነው ብለዋል።
ተቋሙ ከዚህ በፊት በቁጥጥር ሥራው ደካማ ነበር ያሉት ምክትል ዳይሬክተሩ አሁን ላይ ተቋማዊ ትኩረትን በማሳደግ እና ከሌሎች አጋሮቹ ጋር በመተባበር አሠራርን ማዘመን ብሎም የሕግ ማዕቀፍ ማሻሻያ በማድረግ ጠንካራ የአሠራር ሥርዓት እየተከተለ መኾኑን ነው የገለጹት።
ዘጋቢ፦ አንዱዓለም መናን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!