
ባሕር ዳር፡ መስከረም 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሥነ-አዕምሮ ባለሙያ፣ አማካሪ እና አሠልጣኝ ዶክተር ምህረት ደበበ በአማራ ክልል ዳኞች ጉባኤ ላይ ተገኝተው ለፍትሕ ሥርዓቱ ስኬት ወሳኝ በኾኑ ጉዳዮች ላይ ሥልጠና ሰጥተዋል።
ንጹሀንን የሚጠብቁት እና ሕግን የሚተላለፉትን የሚቀጡት አመኔታን ያተረፉ የዳኝነት ተቋማት መኾናቸውን ዶክተር ምህረት ገልጸዋል።
“የመተማመን ብርታት ለፍትሕ ሥርዓት” እና “ምልዓት ያለው ሕይወት ለፍትሕ ሥርዓት ማንሰራራት” በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ተደርጎ ነው ሥልጠና የተሰጠው።
መተማመን በግለሰቦች፣ በማኅበረሰብ እና በተቋማት መካከል ለውጤታማ ሥራ እና ሰላማዊ ኑሮ ወሳኝ መኾኑን ዶክተር ምህረት አብራርተዋል።
ለፍትሕ ፈላጊው ቀልጣፋ እና አጥጋቢ ምላሽ ለመስጠት በዳኞች እና በተገልጋዩ መካከል መተማመን የሞላበት ግንኙነት መኖር አለበትም ብለዋል።
ወደ ፍርድ ቤት የሚመጡ ባለጉዳዮች አካላዊ ጉዳት የደረሰባቸው፣ ላባቸውን ያፈሰሱበትን ሃብት የተቀሙ እንደኾኑ ጠቅሰዋል።
በመኾኑም ዳኞች ለተበዳዮች ትክክለኛ ዳኝነት በመስጠት፣ ለችግሮቹ መፍትሄ መኾን አለባቸው ነው ያሉት።
መፍትሄውም በታማኝ፣ ቀልጣፋ፣ ተገማች እና ትክክለኛ የዳኝነት ሥርዓት ሊመጣ እንደሚችልም አጽንኦት ሰጥተዋል።
ዳኞች በዳኝነት ዕውቀት እና ሥነ-ምግባር ታንጸው ትክክለኛ እና ተገማች ውሳኔዎችን ማሳለፍ እንዳለባቸውም ገልጸዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ሥልጠናው በሥራቸው እና በግል ሕይወታቸው ላይ ተጨባጭ ለውጥ እንደሚያመጣ መናገራቸውን ከክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተገኘው መረጃ ያሳያል።
በክልሉ ፍርድ ቤቶች ታሪክ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተሳታፊ ተሠብሥቦ በለውጥ እና ማሻሻያ መንገዶች ላይ ሲመክር ይህ የመጀመሪያው መኾኑን በመግለጽ ምሥጋናም አቅርበዋል።
የአማራ ክልል ፍርድ ቤቶች ዳኞች ጉባኤ ዛሬም ለሦሥተኛ ቀን የሚቀጥል ነው። የክልሉ የ25 ዓመት የፍትሕ አሻጋሪ ፍኖተ ካርታ ቀርቦ ውይይት ይደረግበታል ተብሎም ይጠበቃል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!