“አረጋውያን ለሀገር ውለታ የዋሉ ናቸው፤ ዕድሜያቸው ስለገፋ በቃችሁ ተብለው የሚተው አይደሉም”

4
ባሕርዳር፡ መስከረም 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሀገር ባለውለታ፣ አስታራቂ፣ ታሪክ ነጋሪ አረጋውያንን መንከባከብ እና መደገፍ ሁላችንም የሚመለከት ጉዳይ ነው። ይህን በጎ ሃሳብ በርካታ ሰዎች በግልም ይሁን በማኅበር በመመስረት ይተገብሩታል። “በጎ እናስብ” በሚል መሪ መልዕክት በወጣቶች የተመሠረተው ድንበር የለሽ በጎ አድራጎት ማኅበር አንዱ ነው።
የድንበር የለሽ በጎ አድራጎት ማኅበር ምክትል ሰብሳቢ ገነት ተመስገን ድንበር የለሽ በጎ አድራጎት ማኅበር አረጋውያንን፣ ወጣቶችን እና ሕጻናትን የመደገፍ ዓላማ ይዞ በ15 ወጣቶች እንደተመሠረተ ነግራናለች። በቅርቡ 12 ዓመት የሚደፍነው ማኅበሩ ቁጥራቸው 100 የሚደርሱ አረጋውያንን በቋሚነት የመንከባከብና የመደገፍ ሥራ እየሠራ እንደኾነም ጠቅሳልናለች።
ሚዲያን በመጠቀም ከሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ በሚኖሩ በጎ ፍቃደኞች ድጋፍ አሰባስቦ በክርስትና እና እስልምና ሃይማኖት ተከታዮች የሚከበሩ ሦስት በዓሎች በየዓመቱ የበዓል መዋያ ድጋፍ እንደሚያደረግም ገልጻልናለች።
እንደ አስፈላጊነቱም የአልባሳት ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው አንስታለች። ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመነጋገር ነጻ የሕክምና አገልግሎት በቋሚነት እንዲያገኙ መደረጉንም ጠቅሳልናለች። የአስቤዛ እና የጤፍ ዱቄት ድጋፍ እንደሚያደርግም አንስታለች። ከመንግሥትም ኾነ ከረጅ ድርጅቶች የሚደረግላቸው ድጋፍ እንደሌለም ጠቁማለች።
ማኅበሩ አረጋውያንን ከመደገፍ ባሻገር ወደሚኖሩበት አካባቢ በመንቀሳቀስ ባሉበት ቤት ለቤት የመንከባከብ ከሁሉም በላይ የሚሠራው ተግባር መኾኑን ጠቅሳለች።
ከሚደገፉት ውስጥ ደጋፊ እና ቤተሰብ የሌላቸው አሉ ነው ያለችን። ያሉበትን ሁኔታ የመጠየቅ፣ የማማከር፣ የሚደገፉትን ዓይነት የመለየት፣ ንጽህናቸውን የመጠበቅ፣ ልብሳቸውን የማጠብ እና ቤታቸው በክረምት ወቅት የሚያስቸግራቸውን ደግሞ የመጠገን እና የማደስ ሥራ እንደሚሠራ አንስታልናለች።
የማኅበሩ መሪ ቃል “በጎ እናስብ” የሚል ነው ያለችን ወጣት ገነት ተመስገን አረጋውያን ለሀገር ውለታ የዋሉ ናቸው፤ ዕድሜያቸው ስለገፋ በቃችሁ ተብለው የሚተው አይደሉም ብላናለች። ትናንትና ብዙ ነገር አሳልፈዋል፤ ብዙ ነገር አድርገው ሀገርን ለወጣቶች አስረክበዋል ብላለች። አረጋውያን ለሚመጣው ትውልድም መሰረት ስለኾኑ በማኅበሩ በቋሚነት ድጋፍ እየተደረገ መኾኑን ጠቅሳለች።
የፋና የሕጻናትና የማኅበረሰብ ልማት ማኅበር ሥራ አስኪያጅ ዳኛቸው ደርሶ ደግሞ በባሕር ዳር ከተማ ከሚገኙት የ”ታትዬ” አረጋውያን ማኅበር እና የባሕር ዳር ተወላጆች አረጋውያን ማኅበር ጋር በጋራ እንደሚሠሩ እና በኀላፊነት እንደሚያስተባብሩ ነግረውናል።
በባሕር ዳር ከተማ ጧሪ፣ ቀባሪ እና ደጋፊ ያጡ አረጋውያንን ከመንከባከብ እና ከመደገፍ አንጻር የወጣቶች ተነሳሽነት እጅግ በጣም አስደሳች መኾኑንም ገልጸዋል። አረጋውያን ምግብ፣ መጠጥ እና አልባሳት ብቻ አይደለም የሚቸግራቸው፤ ልጅም ይቸግራቸዋል፤ አምስት እና ከዛ በላይ ልጆች ወልደው ሁሉንም በሞት ያጡ አሉና ልጅ ልንኾናቸው ይገባልም ብለዋል።
ካገኙ በጎረቤት የቡና ቁርስ የሚውሉ፣ ካጡ ደግሞ እንዲሁ ቁጭ የሚሉ፣ እኛን ያሳደጉ አረጋውያን በየአካባቢያችን አሉ ነው ያሉት። አረጋውያን የሀገር ቅርስ እና የሀገር ምሰሶዎች ናቸውም ብለዋል። የጡት እናት እና አባት እንዲሁም የጡት ልጅ የሚለውን ባሕል በመመለስ አንድ ሰው አንድ አረጋዊ እንዲይዝ እየተደረገ እንደኾነም ገልጸውልናል።
የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር በጎ ፈቃደኛ አባላት ያሏቸው አረጋውያንና ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚደግፉ ማኅበራት በየአካባቢው እየተመሰረቱ መኾኑንም ጠቅሰዋል።
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገኙ ወጣቶችን ጨምሮ በርካታ ወጣቶች እና በጎ አሳቢዎች የአረጋውያንን ልብስ ማጠብ፣ ቤታቸውን ማጽዳት፣ መንከባከብ፣ መጠየቅ እና መሰል ተግባራት መከወን ላይ ተሳትፎ እያደረጉ እንደኾነም አንስተዋል።
አረጋውያን ወደ ማዕከል እንዲገቡ ሳይኾን አካባቢያቸውን እና ጎረቤቶቻቸውን ሳይለቁ ድጋፍ እና እንክብካቤ እንዲደረግላቸው ፍላጎት አለን ያሉት ሥራ አስኪያጁ አረጋውያን ቋሚ የኾነ ገቢ እንዲኖራቸው እንደ ከተማ እየተሠራ ነውም ብለዋል።
ለአረጋውያን የድጋፍ ብቻ ሳይኾን የልጅ ናፍቆት እና ርሀብም አለ፤ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ እየሠራን አንድ ሰው አንድ አረጋዊ እንዲይዝ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል። የገቢ ምንጭ ፈጥሮ በቋሚነት ለመደገፍም በባሕርዳር ከተማ ግሽ አባይ ክፍለ ከተማ ለጊዜው በ1 ሺህ ካሬሜትር ቦታ ላይ የገቢ ምንጭ ለማምጣት የከተማ ግብርና ሥራ ጀምረናል ነው ያሉት። ዳቦ ቤት እና ወፍጮ ቤትም ተከፍቷል ብለዋል።
መንግሥትም ኾነ አረጋውያንን ለመደገፍ የተመሰረቱ ማኅበራት ሁሉንም አረጋውያንን መደገፍ ስለማይችሉ ገቢ በማመንጨት በቋሚነት የመደጋገፍ ባሕሉን የሚያስቀጥል ኮሚቴ በማዋቀር እንደከተማ እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል።
እማሆይ አበሩ ካሴ ፋና የሕጻናትና የማኅበረሰብ ልማት ማኅበር ድጋፍ የሚያደርግላቸው የ80 ዓመት አረጋዊ ናቸው። አካል ጉዳተኛ እና የሚደግፍ ልጅ እንደሌላቸው ነግረውናል። “ወድቀው ተነስተው ድጋፍ እያደረጉልኝ ያሉ ወጣቶች ናቸው” ነው ያሉን።
በማኅበሩ አማካኝነት በየወሩ በቋሚነት የ1 ሺህ ብር ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደኾነም ጠቅሰዋል።
ወይዘሮ መልካም እንዳለው ደግሞ የድንበር የለሽ በጎ አድራጎት ማኅበር እንክብካቤ እና ድጋፍ ከሚያደርግላቸው አረጋውያን መካከል አንዷ ናቸው። ልጆች ቢኖሯቸውም የተወሰኑት አብረዋቸው እንደማይኖሩ እና ያሉትም ርሳቸውን መደገፍ የሚችሉ እንዳልኾኑ ነግረውናል።
ድንበር የለሽ በጎ አድራጎት ማኅበር በበዓላት ጊዜ የበዓል መዋያ የሚኾን ድጋፍ ሲያደረግላቸው እንደነበር አስታውሰዋል። የአልባሳት ድጋፍ ተደርጎላቸው እንደነበረም ጠቅሰዋል። በየጊዜው ባሉበት ቦታ በመሄድ እንደሚጠይቋቸውም ነግረውናል።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየብሔረሰብ አሥተዳደሩን ሰላም ማጽናት ተችሏል።