
ሰቆጣ: መስከረም 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ ምክር ቤት 4ኛ ዙር 12ኛ ዓመት 31ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ነው።
የምክር ቤቱን ጉባኤ የከፈቱት የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንታይቱ ካሴ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ዐሻራ ያረፈበት የአንድነታችን ማመሳከሪያ የኾነው የታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ በመመረቁ እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል።
ባለፈው በጀት ዓመት በኢኮኖሚያዊ፣ በማኅበራዊ እና በመልካም አሥተዳደር ዘርፎች አበረታች ተግባራት መከወናቸውን ያስታወሱት አፈ ጉባኤዋ የዘመናት ጥያቄ የነበረው ከብልባላ ሰቆጣ የአስፋልት መንገድ መጀመር እና በፌዴራል እና በክልሉ መንግሥት የሚሠሩ ሜጋ ፕሮጀክቶች በጥራት እየተሠሩ መኾናቸውን እንደማሳያነት ጠቁመዋል።
በክልሉ የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር ለመፍታት ብሔረሰብ አሥተዳደሩ የበኩሉን ሚና ተወጥቷል ያሉት ወይዘሮ ፋንታይቱ ካሴ በዋግ ኽምራ ያለውን አንጻራዊ ሰላም ማጽናትም ተችሏል ብለዋል።
በምግብ ራስን ለመቻል እና የሚሰደዱ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ለመቀነስ መሠራት ያሉባቸው ሥራዎችን በተመለከተ እና ፕሮጀክቶችን በጥራት እና በአፋጣኝ ከማስፈጸም አኳያ የምክር ቤት አባላቱ ጥያቄ አንስተዋል።
ከምክር ቤት አባላት ለተነሳው ጥያቄ ምላሸ የሰጡት የኢንቨስትመንት መምሪያ ኀላፊ እና ምክትል አሥተዳዳሪ ሹመት ጥላሁን በ2017 በጀት ዓመት ብሔረሰብ አሥተዳደሩ በሁለንተናዊ ዘርፍ ጥሩ አፈጻጸም አስመዝግቧል ብለዋል።
በግብርናው ዘርፍ በተለይም በአትክልት እና ፍራፍሬ ገበያውን ከማጥገብ ባለፈ ለአጎራባች ከተሞች ጭምር ማቅረብ የሚችል ሥራ መሠራቱን አንስተዋል።
ምክትል አሥተዳዳሪው በቀጣይ በተቀናጀ መንገድ ከተሠራ ለውጥ ማስመዝገብ እንደሚቻልም አረጋግጠናል ነው ያሉት።
የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሠራ ቢኾንም በ2018 በጀት ዓመት ተጀምረው የተጓተቱ ፕሮጀክቶችን በልዩ ክትትል እና ድጋፍ ማጠናቀቅ እንደሚገባም አሳስበዋል።
የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ ምክር ቤት መስከረም 22/2018 ዓ.ም ጉባኤውን ሲቀጥል የብሔረሰብ ምክር ቤቱን የ2018 በጀት ዓመት የፋይናንስ ዕቅድ ሪፖርት እና የብሔረሰብ አሥተዳደሩን የ2018 በጀት መርምሮ ማጽደቅ በሚሉ አጀንዳዎች ዙርያ ይመክራል ተብሎ ይጠበቃል።
ዘጋቢ፦ደጀን ታምሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!