የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ዓለም አቀፍ የውኃ ድንጋጌን ያከበረ ነው።

4
ባሕር ዳር: መስከረም 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ለሺህ ዓመታት የቀይ ባሕር ገናና ባለቤት የነበረችው ኢትዮጵያ በታሪክ አጋጣሚ የነበራትን የባሕር በር አጥታ ቆይታለች።
አሁን ላይ ኢትዮጵያ የጥንት የባሕር ባለቤትነቷን ለማግኘት ጥያቄ አቅርባለች። እያነሳችው ያለው የባሕር በር የጋራ ተጠቃሚነት ጥያቄ ፍትሐዊ እና መርህን የተከተለ ሐቅ ነው ይላሉ ምሁራን።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር እና የሦሥተኛ ድግሪ ተማሪ ትዕዛዙ አያሌው የባሕር በር ለሀገራት ሁለንተናዊ ምልዑነት መሠረታዊ ነገር ነው ብለዋል። ዓለም አቀፍ ባሕር ለሁሉም የሰው ልጆች አገልግሉት መስጠት እንዳለበትም በዓለም አቀፍ ሕግ የተደገፈ ነው ይላሉ።
ሀገራት ተፈጥሮን በፍትሐዊነት ይጠቀሙ ዘንድ ሕጉ ይደነግጋል ነው ያሉት። በዚህም እ.አ.አ 1982 ላይ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓለም አቀፍ የውኃ አጠቃቀምን አስመልክቶ ያወጣው ድንጋጌ ተጠቃሽ እንደኾነ ነው የተናገሩት።
ይህ የሕግ ድንጋጌ ባሕር የሚባለውን ክፍል ከአጠቃቀም አንጻር በሦስት ከፍሎ አስቀምጦታል ብለዋል። ይህም ሀገራት ውኃን እንዴት መጠቀም እንዳለባቸው እና የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት በምን መንገድ ተጠቃሚ መኾን እንደሚችሉ የሚያሳይ ድንጋጌ እንደኾነ ነው የገለጹት።
በባሕር ዳርቻ ያሉ ሀገራት ከደረቁ መሬት አንስቶ ከ20 እስከ 25 ኪሎ ሜትር ድረስ ሉዓላዊ ግዛታቸው እንደኾነ ሕጉ ያስቀምጣል ነው ያሉት። ከባሕር ዳርቻው አንስቶ እስከ 330 ማይል ድረስ ደግሞ የኢኮኖሚ ዞናቸው ማድረግ እንደሚችሉም ሕጉ አመላክቷል ብለዋል። ይህ ሲኾን ግን በሉዓላዊነት ይይዛሉ ማለት አይደለም ነው ያሉት። የኢኮኖሚ ተጠቃሚ መኾን እንደሚችሉ ነው የሚገልጸው ብለዋል።
በኢኮኖሚ ዞን ከሚካለለው ውጭ ያለው የባሕር ክፍል ግን ከማንም ነጻ ኾኖ የዓለም ሁሉ ሀብት እንደሚኾንም ይደነግጋል ነው ያሉት። ሁሉም ሀገራት በዚያ የተፈጥሮ ሀብት ላይ መጠቀም እንደሚችሉም አንስተዋል።
የባሕር በር የሌላቸውን ሀገራት በተመለከተ ዓለም አቀፍ ሕጉ መፍትሔ ያስቀመጠ እንደኾነም ገልጸዋል። ሀገራት ምንም እንኳ ከባሕሩ ጋር ቀጥታ የተገናኙ ባይኾንም በአስተላላፊ ሀገራት አማካኝነት የተፈጥሮው ተጠቃሚ እንዲኾኑ ያስቀመጠ ነው ይላሉ።
አስተላላፊ የተባሉት ሀገራትም የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት እነሱን አልፈው የባሕሩ ተጠቃሚ መኾን እንዲችሉ ማድረግ እንዳለባቸው ሕጉ ያስቀምጣል ብለዋል። በሉዓላዊነት ባሕሩን ባይዙ እንኳ መተላለፊያ መስጠት ግዴታቸው እንደኾነ የዓለም አቀፍ የውኃ አጠቃቀም ድንጋጌው ላይ እንደተቀመጠ ነው የገለጹት።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት የመኾን ጉዳይ በዓለም አቀፍ ሕጉ ብቻ የሚታጠር እንዳልኾነ አንስተዋል። ባሕሩን መጠቀም የሚቻለው አንድም በሉዓላዊነት መንገድ ነው፤ ሌላው ደግሞ በዓለም አቀፍ ሕጉ መሠረት በአስተላላፊ ሀገሮች ላይ ሄዶ የተፈጥሮው ተጠቃሚ በመኾን ይኾናል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ጥያቄም በአስተላላፊ ሀገሮች አማካኝነት የባሕር በሩ ተጠቃሚ መኾን እንዳለ ኾኖ የሉዓላዊነት ተጠቃሚነትንም የሚጨምር ፍትሐዊ ጥያቄ እንደኾነ ነው ያነሱት። ኢትዮጵያ ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ በተሠራ ታሪካዊ ስህተት የባሕር በር አልባ ኾና ትገኛለች ያሉት ምሁሩ ባሕሩን ያጣንበት መንገድ ከጅምሩ ከፍትሕ ያፈነገጠ ነበር ይላሉ።
“ኢትዮጵያ በታሪክ ከባሕር በር የወጣችበት መንገድ ከቅጥር ግቢ ወጥቶ በአውራ ጎዳና መጓዝ እንደ መከልከል ያህል ነው” ብለዋል። ኢትዮጵያ የባሕር በር የምትፈልገው ለተራ የንግድ እንቅስቃሴ ሳይኾን ስትራቴጂካዊ የኾነ እና የወደፊት እጣ ፈንታዋን ሊወስን የሚችል መሠረታዊ ነገርን ይዛ መነሳቷን ተናግረዋል።
ለሀገሪቱ የቀጣይ እድገትም ኾነ ለሉዓላዊነት እና ደኅንነት ጥያቄው ፍትሐዊ እና ሕጋዊ መሠረት ያለው እንደኾነም ጠቁመዋል። ጥያቄዋ ዓለም አቀፍ የውኃ ድንጋጌን የማይጣረስ እንደኾነም አስረድተዋል።
በራሳችን ሉዓላዊነት የምናሥተዳድረው የባሕር በር የማግኘት ጉዳይ እንዲሁ በተራ የሚነገር ሳይኾን ትልቅና መሠረታዊ አጀንዳ ነው ይላሉ። አስፈላጊነቱም ጥልቅ ነው ብለዋል።
የአዋጭነት ስሌትን አንግቦ መንቀሳቀስ ብልጠት መኾኑንም አንስተዋል። የወቅቱን የዓለም የጂኦ ፖለቲካ አሰላለፍ በሚገባ ማጤን፣ የዲፕሎማሲ ወቅታዊ አቋምን መፈተሽ እና የኃይል ሚዛንን ግምት ውስጥ ማስገባት ተገቢ እንደኾነ ተናግረዋል።
ዓለም አሁን ላይ በዓለም አቀፍ ሕግ የመመራቷ ነገር መጤን አለበት ነው ያሉት። ውጫዊ እና ውስጣዊ የራስ ጤንነትንም መመልከት ብልህነት ነው ብለዋል።
የአዋጭነት ስሌትን በሚገባ ማየትም ሳይንስ እንደኾነ ነው የተናገሩት። “ዓለም አቀፍ ሕግን ብቻ ሳይኾን ዓለም አቀፍ ግንኙነትንም መፈተሽ ያስፈልጋል” ነው ያሉት።
ዘጋቢ:- ሰለሞን አንዳርጌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article” ከጎዳና ላይ ስላነሱን ደስ ብሎኛል” ከጎዳና የተነሳ ታዳጊ
Next articleየብሔረሰብ አሥተዳደሩን ሰላም ማጽናት ተችሏል።