
ባሕር ዳር: መስከረም 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመኾን የጎደና ልጆችን ከጎዳና በማንሳት ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲገቡ አድርጓል።
መምሪያው የጎዳና ልጆችን የተለያዩ ግንዛቤዎችን በመፍጠር እና ሥልጠናዎችን በመስጠት ከጎዳና በማንሳት ወደ ቤተሰቦቻቸው የማቀላቀል ሥራ ይሠራል።
የባሕርዳር ከተማ ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ሰብለ ዘውዱ ሕጻናት የነገ ሀገር ተረካቢ እና የነገዋ ኢትዮጵያን እጣ ፈንታ ወሳኝ በመኾናቸው ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል እንደራሱ ልጅ ማየት ይገባዋል ነው ያሉት።
“አንድም ሕጻን ከትምህርት ገበታ ውጭ መኾን የለበትም” በሚል መሪ መልዕክት የድርሻቸውን እየተወጡ መኾኑንም ጠቁመዋል፡፡
ዛሬ 70 የጎዳና ልጆች እና ለማስተማር የአቅም ውስንነት ካለባቸው ቤተሰቦች የተውጣጡ ሕጻናት ሙሉ የትምህርት ወጭያቸው ተሸፍኖላቸው ወደ ትምህርት ቤት እንዲገቡ የማድረግ ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል።
ወደ ቤተሰብ ለሚቀላቀሉትም የሦሥት ወር የሥነ ልቦና ዝግጅት እና የተለያዩ ሥልጠናዎች ለመስጠት ጥረት እየተደረገ መኾኑንም አስረድተዋል።
ትምህርት ለሚማሩትም ሙሉ ወጫቸው ተሸፍኖላቸው እንዲማሩ ዕድሉ ተመቻችቶላቸዋል ነው ያሉት፡፡አስፈላጊው ድጋፍ ተደርጎ ወደ ቤተሰባቸው ከሚቀላቀሉት ውስጥ 30ዎቹ ሴቶች ሲኾኑ 40ዎቹ ወንዶች ናቸው፡፡
የጎዳና ሴት ሕጻናት መከላከያ ተሀድሶ እና ማቋቋሚያ ድርጅት ( OPRIFS) አሥተባባሪ ሀብታም ሲራክ ድርጅታቸው በክልሉ ከ16 ዓመት በላይ እና ከ18 ዓመት በታች የኾኑ ሴት ታዳጊዎችን ወደ ማዕከል በማስገባት የተለያዩ አገልግሎቶችን እየሰጡ መኾኑን ተናግረዋል።
ዛሬ የተረከቧቸው 30 ሴት ሕጻናት ድርጅቱ ከሚከውናቸው ተግባራት አንዱ መኾኑን አብራርተዋል።
አስተባባሪዋ ከሴቶች እና ሕጻናት መምሪያ ጋር በመተባበር ለሕጻናቱ እንክብካቤ ለመስጠት ፈርመው መረከባቸውንም ጠቁመዋል።
ተቋሙ ለልጆቹ የሦሥት ወራት የተሀድሶ አገልግሎት ከሰጠ በኋላ ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲቀላቀሉ የማድረግ ሥራ ይሠራልም ነው ያሉት፡፡
ወደ ቤተሰቦቻቸው መመለስ የማይፈልጉ ሴቶችን ደግሞ የተወሰነ መቋቋሚያ በመስጠት ወደ ሥራ ተሰማርተው እራሳቸውን እንዲያግዙ የማድረግ ሥራ ይሠራል ብለዋል፡፡
የሕዝብ አንባ በጎ አድራጎት ድርጅት መሥራች ማሩ ደስታ
40 ወንድ ልጆችን መረከባቸውን ገልጸዋል። ድርጅቱ ራሱን እያለማ ሀብት በመፍጠር ወገኖቹን የሚደግፍ ነው ብለዋል።
ድርጅቱ ከዚህ በፊት ከቤተሰባቸው ተፈናቅለው ጎዳና ላይ የወጡ ልጆችን ወደ ቤተሰብ የመቀላቀል እና የትምህርት ግብዓት ችግር ያለባቸውን ደግሞ ያግዝ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
ዛሬ 40 የሚኾኑ ወንድ ተማሪዎችን ከሴቶች እና ሕጻናት መምሪያ ጋር ውል በመውሰድ ውጤት አምጥተው ዩኒቨርሲቲ እስከሚገቡበት ድረስ ለመደገፍ መቀበላቸውን አብራርተዋል፡፡
ተቋሙ ይህንን ሲያደርግ የመጀመሪያው መኾኑን የተናገሩት መሥራቹ ልጆቹ ከጎዳና ሕይወት የመጡ በመኾናቸው ከሥነምግባር ማስተካከል ጀምሮ ብዙ ሥራ መሥራት እንደሚጠይቅም ተናግረዋል፡፡
ዛሬ በተቀበሏቸው ልጆች ውጤታማ ከኾኑ በቀጣይ ይህንን አጠናክረው እንደሚሠሩም ተናግረዋል፡፡
ዕድሉን ካገኙ የጎዳና ልጆች መካከል መኩሪያው ሽዋጋው ወላጆቹን ማጣቱን ገልጸዋል።
በጎዳና ላይ መኖር በጣም አስቸጋሪ መኾኑን ለአሚኮ የተናገረው ታዳጊው በበጋ ፀሐዩ በክረምት ደግሞ ዝናቡ ያስቸግራቸው እንደነበር ተናግሯል።
“ዛሬ ከጎዳና ላይ እኛ አለን መማር የምትፈልጉ ከኾነ ኑ እናስተምራችሁ ብለው ይዘውን ሲመጡ በጣም ነው ደስ ያለኝ” ብሏል፡፡
የሁልጊዜም ሕልሙ ትምህርት መማር እንደነበር ተናግሯል። እንዲህ የሚያስብልን ወገን ይኖረናል የሚል ሃሳብ አልነበረንም ነው ያለው።
አሁን ያገኘሁትን ዕድል ተጠቅሜ ትልቅ ደረጃ በመድረስ እንደኔ ጎዳና ያሉ ልጆችን በማንሳት እና በማስተማር የበኩሌን ለመወጣት እራሴን አዘጋጅቻለሁ ብሏል፡፡
ሌላኛዋ ታዳጊ እመቤት ጌታቸው በችግር ምክንያት ትምህርቷን ማቋረጧን ገልጻለች፡፡ “በተሰጠኝ ዕድል በጣም ደስተኛ ነኝ” ብላለች። ወደፊትም ጠንክሬ በመማር ዛሬ እኛን ከችግር በማንሳት ሊያስተምሩን እንደፈቀዱ ድርጅቶች ሁሉ መማር እየፈለጉ አቅም ያጡ እህት እና ወንድሞቸን እደግፋለሁ ነው ያለችው።
ዘጋቢ፦ ሰናይት በየነ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!