
ባሕር ዳር: መስከረም 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ከሰሜን ጎጃም ዞን ፍትሕ መምሪያ እና በስሩ ከሚገኙ የፍትሕ ጽሕፈት ቤቶች ኀላፊዎች እና አቃቤያነ ሕግ ጋር በ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ውይይት አካሂዷል። ባለፈው በጀት ዓመት የነበሩ ስኬቶች እና ድክመቶችም ቀርበዋል።
የሰሜን ጎጃም ዞን ፍትሕ መምሪያ ኀላፊ ሰጥአርጌ መሰሉ እንዳሉት በ2017 በጀት ዓመት በዞኑ በወንጀል እና ፍትሐ ብሔር አገልግሎት፣ በሰነዶች፣ በጠበቆች እና በመሰል አገልግሎቶች ላይ ትኩረት ተደርጎ ሲሠራ ቆይቷል። በበጀት ዓመቱ በቀረቡ ጉዳዮች ላይ የአቃቤያነ ሕግ ፈጥኖ የመወሰን፣ በፍትሐብሔር እና በወንጀል ጉዳዮች ላይም ተከራክሮ ማሸነፍ አቅም እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።
የመንግሥትን እና የሕዝብን መብት እና ጥቅም በማስከበርም የተሻለ ሥራ መሥራት መቻሉን ገልጸዋል። በተለይም የወንጀል ጉዳዮችን ተከታትሎ በማጣራት እና አጥፊዎችን ተጠያቂ የማድረግ ሥራ መሠራቱን አንስተዋል።
በበጀት ዓመቱ ከ25 ሚሊዮን በላይ ብር
በወንጀል የተመዘበረ የመንግሥት ሀብት በድርድር እና በክስ ማስመለስ እንደተቻለም ገልጸዋል።
ዞኑ በበጀት ዓመቱ ባከናወነው ሥራ በክልሉ ከሚገኙ 14 የፍትሕ መምሪያዎች ሁለተኛ ደረጃ ላይ መቀመጡን ገልጸዋል።
በ2018 በጀት ዓመት የነበሩ ጥንካሬዎችን በማስቀጠል፣ ድክመቶችን በማሻሻል ከባለፈው ዓመት በተሻለ ለመፈጸም ባለሙያዎች ጋር ውይይቶች መደረጋቸውን ገልጸዋል።
የውይይቱ ተሳታፊ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ፍትሕ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አማርከኝ ዮሴፍ ባለፉት ሁለት ዓመታት በክልሉ የተከሰተው የጸጥታ ችግር በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን ገልጸዋል። በተከሳሽ እና ምስክር አቀራረብ ችግር ምክንያት በሚዘጉ መዛግብት ማኅበረሰቡ በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ የነበረውን አመኔታ እንዲቀንስ አድርጓል ብለዋል።
ማኅበረሰቡ ለፍትሕ ተቋማት ይሰጥ የነበረውን ጥቆማ ጭምር መቀነሱን ነው ያነሱት። በክልል ደረጃ የታቀዱ እቅዶች ከዚህ በፊት የታዩ ችግሮችን የሚቀርፉ መኾናቸውን ገልጸዋል።
በባሕር ዳር ከተማ ፍትሕ ጽሕፈት ቤት የሰነዶች የሥራ ሂደት ኀላፊ ትዕግሥት አንዳርጌ ባለፉት ዓመታት የተከሰቱ ችግሮች በፍትሕ አሠራሩ ላይ እንቅፋት ኾኖ መቆየቱን ገልጸዋል።
የፍትሕ ተቋማት አሠራርን በማዘመን የአገልግሎት አሰጣጡን ማቀላጠፍ የበጀት ዓመቱ ትኩረት ኾኖ ተቀምጧል።
ዘጋቢ:- ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!