የአማራ ክልል መንግሥት ሙስናን ለመታገል ቁርጠኛ አቋም ይዟል።

11
ባሕር ዳር: መስከረም 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የሥነ ምግባር ግንባታ እና የጸረ ሙስና ትግል ጥምረት የ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸሙን ገምግሞ የ2018 በጀት ዓመት እቅዱ ላይ ተወያይቷል።
የጥምረቱ አባል ተቋማት በአርዓያነት ቀድመው እንዲያቅዱ፣ ክልሉ ካለበት የሙስና ችግር አኳያ ከፍተኛ ሥራ ታቅዶ መሠራት አለበት፣ በተፈጠረው ግንዛቤ እና ሙስናን የመከላከል ሥራ ምን ውጤት እንደተገኘ መለካት እንደሚገባ፣ የተቋማት ሥራም መለኪያ ሊኖር እንደሚገባው፣ ሙስናን ለመከላከል ቴክኖሎጂን የተጠቀሙ ተቋማትን ማጠናከር እንደሚገባ፣ በተጓዳኝም ተጠያቂነትም እንዲተገበር ነው አስተያየት ሰጪዎች የተናገሩት።
የጥቆማ ሥርዓት እንዲጠናከር እና ጥብቅ የሕግ እርምጃ መውሰድም ለመከላከሉ ሥራ አጋዥ እንደኾነ ተነስቷል። የአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ፋሲል ታዬ የሃይማኖት ተቋማት ሥነ ምግባር ግንባታ እና ሙስናን መከላከል ቀዳሚ ሥራቸው መኾኑን ገልጸዋል። የሃይማኖት አባቶች ለተከታዮቻቸው ከሚያስተምሩት ሃይማኖታዊ አስተምህሮ በተጨማሪ ለተከታዮቻቸው ሥነ ምግባርን እንደሚቀርጹ ተናግረዋል።
የሃይማኖት ጉባኤ አባላትም ከመደበኛው አስተምህሯቸው በተጨማሪ ሙስናን ስለመከላከል ለማስተማር ተሞክሯል። በሥነ ምግባር ግንባታ ላይ የበለጠ ትኩረት እንዲሰጡ መደረጉንም ነው አቶ ፋሲል የገለጹት።
ምዕመናን ቅዱስ ሕይወትን ለመኖር ሥነ ምግባርን እንዲላበሱ እና ሙስናን የሚጠየፍ እና የሌላውን የማይፈልግ ትውልድ ለመፍጠር የሃይማኖት ተቋማት ኀላፊነቱም፣ እድሉም አላቸው ብለዋል።
የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኀላፊ ክብረት ማሕሙድ በበኩላቸው ባለፈው በጀት ዓመት በተቋማቸው ለተገልጋዩ ሕዝብ እና ለሠራተኞች ብልሹ አሠራር እንዳይፈጠር የግንዛቤ ፈጠራ እንደሚሠራ ገልጸዋል። ለሙስና የሚያጋልጡ አሠራሮችን በማዘመን ችግሩን ለመቅረፍ እየሠሩ መኾኑንም አንስተዋል።
አንዳንድ የሥነ ምግባር ችግር ያለባቸው ባለሙያዎች ያልተገባ ግንኙነት በመፍጠር የተቋሙን ሥራ የሚያደናቅፉ እና የመንግሥትን ገቢ የሚቀንስበት ኹኔታ አለ፤ ችግሩ ከግንዛቤ እና ከአመለካከት ችግር የሚመነጭ ነው፤ በመፍትሄነትም ለሠራተኞች የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
በግንዛቤ ፈጠራው የማይመለሱትን የተለያዩ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ገልጸዋል።
ብልሹ አሠራርን እና ሙስናን ለመታገል የአሠራር ሥርዓቱን በማዘመን ፈጣን ዲጂታላይዝድ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ጠቅሰዋል። በ2018 በጀት ዓመትም ይህ አሠራር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው አቶ ክብረት የገለጹት።
በአማራ ክልል ምክር ቤት የዋና አፈ ጉባኤ ልዩ አማካሪ ደብረወርቅ ይግዛው የጥምረቱ አባላት ለሥራው ትኩረት መስጠት እና በአርዓያነት መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
መጪው ትውልድ የበለጠ ከመጎዳቱ በፊት ችግሩን ከወዲሁ መከላከል የአሁኑ ትውልድ እና ተቋማት ኀላፊነት መኾኑንም ጠቅሰዋል።
የእምነት ተቋማት ትውልድን በሥነ ምግባር በመቅረጽ በኩልም ትልቅ ኀላፊነት ስላለባቸው የበለጠ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ነው ወይዘሮ ደብረወርቅ የገለጹት።
የአማራ ክልል ሥነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ሀብታሙ ሞገስ ጥምረቱ የተቋቋመው የሥነ ምግባር ግንባታ እና ጸረ ሙስና ትግሉን ለማጠናከር እንደኾነ ገልጸዋል።
ሁሉም ተቋም ለሥራው ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚጠበቅበት ነው ኮሚሽነሩ የገለጹት። ከክልሉ የ25 ዓመት አሻጋሪ እድገት እና ዘላቂ ልማት እቅድ ከአምስቱ ተግባራት ውስጥ አንዱ በሥነ ምግባር የታነጸ ትውልድ መገንባት መኾኑን አንስተዋል።
በውይይቱ የተነሱት ውስንነቶችን በማረም በ2018 በጀት ዓመትም ራሱን ችሎ በትኩረት እንደሚሠራ ገልጸዋል።
ሙስና የማይፈጸምበት አካባቢ ባይኖርም በልዩ ርብርብ የሚተኮርባቸው ተቋማት መኖራቸውን ነው ኮሚሽነሩ የጠቆሙት።
ኀላፊዎች ራሳቸውን ከሙስና አጽድተው ለሌላውም አርዓያ እንዲኾኑ እና ሙስናን ለመታገል የሚያስችል ንጽህና እና ብቃት እንዲኖራቸው ይጠበቃል ነው ያሉት።
መንግሥት ሙስናን ለመታገል ቁርጠኛ መኾኑን ያነሱት ኮሚሽነር ሀብታሙ ዲጂታላይዜሽንን ለመጠቀም እና የአንድ ማዕከል አገልግሎትን አጠናክሮ መሥራት እንደሚገባም ገልጸዋል።
ትግሉን በሕጋዊ ማዕቀፍ ለማጠናከር አጋዥ ሕጎች መውጣታቸውን ጠቅሰዋል።
በቀጣይ ሁሉም ተቋማት ከሠራተኞች ጋር የጋራ የተደረገ እቅድ ማዘጋጀት፣ የሥነ ምግባር ትምህርት መስጠት፣ ለብልሹ አሠራር የሚያጋልጡ ክፍተቶችን መድፈን፣ ቴክኖሎጂ አጠቃቀምን አጠናክሮ መቀጠል እና ቅንጅታዊ አሠራርን ማጠናከር እንደሚገባ አሳስበዋል።
ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleመስጠት ላሰበ እና ከውስጡ ለሻተ ብዙ የሚሰጥ ነገር አለ።
Next articleጤና ሚኒስቴር ለቀጣዮቹ አምስት ዓመታት የሚቆየውን ሁለተኛው የኢትዮጵያ ብሔራዊ የጤና ደህንነት ትግበራ ይፋ አደረገ።