
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 05/2012 ዓ.ም (አብመድ) የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በመላው ዓለም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕፃናትን ወደ ጉልበት ሥራ እንዲገቡ ሊያስገድዳቸው እንደሚችል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አሳስቧል፡፡
የወረርሽኙን መስፋፋት ተከትሎ ብዙዎች ሥራ አጥ እየሆኑ፣ ገቢያቸውም እየቀነሰ መሆኑን ያስታወሰው ተመድ ይህም የወላጆቻቸው የገቢ ምንጮች እንዲነጥፉ ምክንያት መሆኑን አስታውቋል፡፡ በዚህም የተነሳ ሁሉም በየፊናው የእለት ጉርስ ፍለጋ መሠማራት ስለሚኖርበት ሕፃናትም ለአቅማቸው የማይመጥኑ የጉልበት ሥራዎችን ለመሥራት እንደሚገደዱ ነው ድርጅቱ ያሳሰበው፡፡
የድህነት መስፋፋት እና የማኅበራዊ አገልግሎቶች አቅርቦት መቀነስም ሕፃናቱ ለጉልበት ብዝበዛ እንዲዳረጉ ከሚያስገድዷቸው ምክንያቶች መካከል ናቸው፡፡
በዚህ ወቅት ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች እርዳታ ማድረግ እንደሚገባም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አሳስቧል፡፡
በተያዘው ዓመት በወረርሽኙ ምክንያት የእንቅስቃሴ ገደብ በመደረጉ የዓለም ኢኮኖሚ በ3 ነጥብ 2 በመቶ እንደሚያሽቆለቁል 250 የዘርፉ ባለሙያዎች መተንበያቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡ ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በፊት የተደረገው ትንበያ ግን የዓለም ኢኮኖሚ ከ2 ነጥብ 3 እስከ 3 ነጥብ 6 በመቶ ዕድገት ሊያስመዘግብ እንደሚችል ነበር ያመላከተው፡፡
እንደ ተመድ መግለጫ በዓለም ዙሪያ ሕፃናት የጉልበት ሠራተኞች ቁጥር (እ.አ.አ) በ2000 ከነበረበት 246 ሚሊዮን አሁን ላይ ወደ 156 ሚሊዮን ቀንሷል፡፡ የወረርሽኙ መስፋፋት ግን የጉልበት ብዝበዛው በእጅጉ እንዲጨምር ምክንያት እንዳይሆን ድርጅቱ አስጠንቅቋል፡፡
በየማነብርሃን ጌታቸው
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡