መስጠት ላሰበ እና ከውስጡ ለሻተ ብዙ የሚሰጥ ነገር አለ።

12
ባሕር ዳር: መስከረም 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ማኅበረሰቡን በጤናው ዘርፍ እያገለገለ የሚገኘው የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪው የሕክምና ባለሙያ ባየው ሞላ ሕዝብን ማገልገል ከሁሉም በላይ ያስደስተኛል ይላሉ።
ሰው እንደየ ተሰጥኦው እና እንደተሰጠው ጸጋ አንዱ ሌላውን ይረዳል የሚለው የሕክምና ባለሙያው መስጠት ላሰበ እና ከውስጡ ለሻተ ብዙ የሚሰጥ ነገር አለ ይላል።
አንዳንድ ጊዜ የምሰጠው የለኝም የሚሉ ሰዎች ብዙ ለሰዎች የሚሰጧቸው ነገር እንዳለ መገንዘብ ይገባቸዋልም ይላል። “እኔ ለአንድ ጉዳት ላጋጠመው ሰው እኔን በማይጎዳ መንገድ ዐይኔን መስጠት እችላለው” ብለዋል።
ዐይን የጉልበት ምርኩዝ ነው ያሉት የሕክምና ባለሙያው ለዚህም ታሳቢ አድርገው ከሕልፈታቸው በኋላ ዐይናቸውን ለዐይን ባንክ ለመለገስ ቃል መግባታቸውን ነው የተናገሩት።
ከህልፈት በኃላ ዐይንን መለገስ ምንም የሚያሳጣው ነገር አይኖርም ያሉት የሕክምና ባለሙያው ባየው ሞላ ለሌላው ጥቅም የሚሰጠው ዐይን ከሕልፈት በኋላ ምስጥ ከሚበላው ማየትን የሚሻው ወንድሜ ቢያይበት መልካም ነው ብለዋል።
ብርሃንን የመሰለ ታላቅ ስጦታ ትኩረት ሊነፈገው አይገባምም ነው ያሉት፡፡
ማኅበረሰቡ ስለ ዐይን ልገሳ ያለው ግንዛቤ አናሳ ነው ያሉት የሕክምና ባለሙያው ባየው ሞላ ይህንን የግንዛቤ ችግር ለመቅረፍ ኅብረተሰቡን የማስተማር ሥራ ማከናወን ይገባል፡፡
ማንኛውም ሰው ከሕልፈት በኋላ የዐይን ብሌኑን በመለገስ ለሌሎች ወገኖቹ ብርሃን እንዲኾኑም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በአማራ ክልል የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ስር የባሕር ዳር ከተማ የዐይን ባንክ ተወካይ እና አስተባባሪ ጠጂቱ ገረመው ዐይን ከሰው ልጅ አምስት የስሜት ሕዋሳት አንዱ ኾኖ በብርሃን ሞገድ አማካኝነት ከዓለማችን መረጃ በመቀበል የማየት ታላቅ ጸጋን ያጎናጽፈናል ይላሉ።
አስተባባሪዋ ዕይታ ለሰው ልጅ ጸዳል የሚያላብስ፣ ከሕይወት ቀጥሎ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው እና ሰውን ከዓለም ጋር የሚያገናኝ ድንቅ ስጦታ ነው ብለዋል።
ይሁን እንጂ በተለያዩ ምክንያቶች ዐይነ ስውርነት በማየት መፈለግ እና ዓለማየት መሐል የቆሙ በርካታ ወገኖችን እየፈተነ እንደሚገኝም አስረድተዋል።
በተለይም የዐይን ብሌን ጠባሳ ሙሉ በሙሉ ማየት የተሳናቸው ሊያደርግ እንደሚችል አስተባባሪዋ ገልጸዋል።
አስተባባሪዋ እንደተናገሩት የባሕር ዳር የዐይን ባንክ ዋና ዓላማ ሊድን በሚችል የዐይን ብሌን ጠባሳ የሚመጣ ዐይነ ስውርነትን መከላከል ነው።
ብርሃን ለሁሉም የሰው ልጆች ይገባል የሚሉት ወይዘሮ ጠጂቱ በማየት መፈለግ እና የማያዩ ብዙ ወገኖች ባሉባት ሀገር ውስጥ የዐይን ንቅለ ተከላ እንዲደረግላቸው የሚሹ በርካታ ኢትዮጵያውያን መኖራቸውን ጠቁመዋል።
የዐይን ብሌን ጠባሳ ሕክምና ሊያገኝ የሚችለው ሰዎች ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ በኋላ በሚለግሱት የዐይን ብሌን አማካይነት ነው።
በመኾኑም ባንኩ በባሕር ዳር ከተማ እና ዙሪያዋ ያለውን ዐይነ ስውርነት ለማጥፋት በርካታ የዐይን ብሌን ለጋሾችን በፈቃደኝነት ለማሠባሠብ እና ቃል ለማስገባት እየሠራ ይገኛል። እስካሁን ድረስም 173 ሰዎች የዐይን ብሌናቸውን ለመለገስ ቃል ገብተዋል።
አስተባባሪዋ ባንኩ ከጊዜ ወደ ጊዜ የፍላጎት እና የአቅርቦት አለመመጣጠን ችግር እየገጠመው መኾኑንም አመልክተዋል።
የዐይን ብሌን ልገሳ ማየት ለሚፈልጉ እና ለሚጓጉ ወገኖች ሕይወት የሚሰጥ ታላቅ ምጽዋት መኾኑን በመገንዘብ ማኅበረሰቡ ከህልፈተ ሕይወት በኋላ የዐይን ብሌን ለመለገስ ቃል እንዲገባም ተቋሙ ጥሪ አቅርቧል።
ተቋሙም ቃል የገቡ ሰዎችን የዐይን ብሌን በመሠብሠብ ንቅለ ተከላውን ለሚያከናውኑ የሕክምና ተቋማት እንደሚያሰራጭም ገልጸዋል።
“የዐይን ብርሃን ለሁሉም የሰው ልጆች ይገባል” የሚለው መልዕክት እውን እንዲኾን ወይዘሮ ጠጂቱ ገረመው ኅብረተሰቡ የዐይን ብሌኑን እንዲለግስ እና የማየት ጸጋን ለወገኖቹ እንዲያጎናጽፍ አበክረው ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፦ ሰመሀል ፍስሀ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleአረጋውያን ታላቅ የሀገር ቅርስ ናቸው።
Next articleየአማራ ክልል መንግሥት ሙስናን ለመታገል ቁርጠኛ አቋም ይዟል።