
ባሕር ዳር: መስከረም 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ትርጓሜ መሠረት አረጋውያን የሚባሉት ዕድሜያቸው 60 ዓመት እና ከዚያ በላይ የኾኑ ሰዎች ናቸው። በአፍሪካ አረጋውያን መብቶች ፕሮቶኮልም ዘንድ ትርጉሙ ተመሳሳይ ነው፡፡ ይህ ትርጉም በኢትዮጵያም ተቀባይነት አግኝቶ እየተሠራበት ነው፡፡
አረጋውያን የዕድሜ ባለጸጋ ናቸው፤ በዕድሜያቸው በርካታ ዕውቀቶች፣ ልምዶች እና ጥበቦችን አግኝተዋል፡፡ በቀለም ትምህርት፣ በኑሮ ሁኔታ እና በተግባር ተምረው፣ አስተምረው ትውልድ አንጸዋል፡፡ እነዚህ አረጋውያን ለሀገር በርካታ ሥራዎችን የሠሩ ባለውለታም ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ብሎም በዓለም አደባባይ ተከብራ የኖረች ሀገር እንድትኾን አረጋውያን ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል። ኢትዮጵያን ለተተኪው ትውልድ ለማቆየት ያልወጡት ዳገት፣ ያለወረዱት ቁልቁለት እንደሌለ ታሪክ ምስክር ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን በነጻነት እና በክብር እንዲኖሩም የሕይወት መስዋዕትነት ከፍለዋል፡፡
አረጋውያን በወጣትነት ዘመናቸው በተለያዩ የሥራ መስኮች ተሠማርተው ሕዝባቸውን እና ሀገራቸውን በማገልገል ለሀገር ውለታ ውለዋል፡፡ በእርጅና ዘመናቸውም በተለይም በማኅበረሰባችን ዘንድ ግጭት ሲፈጠር በማስታረቅ እና ሰላም በማምጣት ይታወቃሉ፡፡
መምህር አትንኩት አባዋ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ እና የአማራ ክልል አረጋውያን ማኅበር አባል ናቸው። አረጋውያን ለሀገር ብዙ የሠሩ፣ ተማሪዎችን በአግባቡ ያስተማሩ መምህራን፣ ወታደር ኾነው ሀገራቸውን ከጠላት የጠበቁ፣ የሃይማኖታዊ አገልግሎት የሰጡ፣ በሁሉም ሙያ ላይ በመሳተፍ በወጣትነት ዘመናቸው ለሀገር ትልቅ ሥራ በመሥራት ውለታ የዋሉ ናቸው ይላሉ።
ለሀገራቸው ብዙ ያገለገሉ ነገር ግን በመንገድ ዳር የወደቁ፣ ረዳት ያጡ በተለያዩ የሥራ መስኮች የሠሩ አረጋውያን አሉ ነው ያሉት፡፡ እነዚህን በወጣትነት ዘመናቸው ለሀገር ትልቅ ሥራ የሠሩ አረጋውያን በአንድ ማዕከል ተሰባስበው ድጋፍ ሊደረግላቸው እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
ተቋማት እና የሚመለከታቸው አካላትም የአረጋውያንን ጉዳይ በባለቤትነት ይዘው የበኩላቸውን አስዋጽኦ ሊያበረክቱ ይገባል ብለዋል፡፡ ወጣቶችም አረጋውያንን መደገፍ እንደሚገባቸው ተናግረዋል።
ሌላው የአማራ ክልል አረጋውያን ማኅበር አባል መምህር ሥራው ይሁን አረጋውያን ባሳለፏቸው የዕድሜ ዘመናቸው በተለያዩ የሥራ መስኮች ተሠማርተው ሀገርን አገልግለዋል ነው ያሉት፡፡
በግላቸው የራሳቸውን ቤተሰብ መሥርተው፣ ልጅ አሳድገው ለቁም ነገር አብቅተዋል፡፡ የሀገር መሠረቱ የቤተሰብ ጽናት እና ጥንካሬ በመኾኑ ለሀገር ባለውለታ ተክተዋል ነው ያሉት፡፡ በተለያዩ የሥራ ዘርፎችም ሀገራቸውን ያገለገሉ በመኾናቸው ለሀገር ባለውለታ ናቸው ብለዋል፡፡ አሁንም በእርጅና ዘመናቸው ለሀገር የሚሠሯቸው ሥራዎች ስላሉ “አረጋውያን ታላቅ የሀገር ቅርስ ናቸው” ነው ያሉት።
አረጋውያን እድሜ የመከራቸው በመኾኑ ንግግራቸው እና ምክራቸው በሙሉ ሰላም መኾኑን አንስተዋል፡፡ ቤተሰብ በፍቅር እና በሰላም እንዲኖር፣ ሰዎች እርስ በእርሳቸው ተግባብተው እና ተስማምተው እንዲኖሩ በመምከር እና በመምራት፣ ግጭት ሲኖር በማስታረቅ ሀገራችን ሰላም እንድትኾን የሚመክሩ እና የሚዘክሩ በመኾናቸው ለሰላም ያላቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡
አረጋውያን ያላቸውን ዕውቀት እና ተሞክሮ ለተተኪው ትውልድ የሚያስተላልፉ በመኾናቸው ቁልፍ የኅብረሰተሰብ ክፍል እንደኾኑም አንስተዋል፡፡
ሁሉም ባይኾኑም ብዙ አረጋውያን በዕድሜ ምክንያት ስለሚደክሙ ጉልበት እና አቅም ስለማይኖራቸው ድጋፍ ይሻሉ፡፡ አሁን አሁን ድሮ የነበረው የመተሳሰብ እና አረጋውያንን የመጦር ባሕል እየላላ በመምጣቱ ብዙዎቹ ጧሪ በማጣት ወደ ልመና እየወጡ እንደኾነ ተናግረዋል፡፡
ኾኖም ካለው ብዛት አንጻር በቂ ነው ባይባልም በማኅበራዊ ዘርፍ እነዚህን የኅብረተሰብ ክፍሎች ለመደገፍ የሚደረገው ጥረት አበረታች ነው ብለዋል፡፡ ለሀገር ብዙ የሠሩ እና ባለውለታ የኾኑት አረጋውያንን በተለያየ መንገድ መደገፍ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል፡፡
የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኀላፊ ንጹሕ ሽፈራው አረጋውያን የሀገር ባለውለታ ናቸው፤ ለትውልዱ ሀገርን፣ እሴትን፣ ባሕል እና ወግን ይዘው ያስተላለፉ ናቸው ብለዋል፡፡ አረጋውያን ዘርፈ ብዙ ተግባራትን የሠሩ የሀገር አለኝታ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡
እነዚህ የሀገር ባለውለታ አረጋውያን በጤና መታወክ፣ በእርጅና፣ በተፈጥሮ እና በሰው ሰራሽ ምክንያቶች ችግሮች ያጋጥሟቸዋል፡፡ ችግሮቻቸውን ለመፍታት፣ ለእነሱ የሚገባቸውን እንክብካቤ እና ፍቅር በመስጠት በኩል ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል መሳተፍ አለበት ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ፍሬሕይወት አዘዘው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!