
ደብረ ብርሃን: መስከረም 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ሸዋ ዞን ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ በግንባታ ላይ በሚገኘው የአረርቲ ማርያም ቤተ ክርስቲያን በደረሰ አደጋ የ30 ሰዎች ሕይዎት ማለፉን የምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።
የፖሊስ ጽሕፈት ቤቱ አዣዥ ዋና ኢንስፔክተር አሕመድ ገበየሁ የአደጋው ምክንያት ለቤተክርስቲያኑ ሕንጻ ግንባታ በተሠራ የእንጨት መወጣጫ ርብራብ ላይ መሸከም ከሚችለው በላይ ሰዎች ለጉብኝት በመውጣታቸው ነው ብለዋል።
በአደጋው የ30 ሰዎች ሕይዎት ወዲያውኑ አልፏል ነው ያሉት።
ከ200 በላይ ሰዎች ከቀላል እስከ ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው ሲኾን ይህም የሟቾችን ቁጥር ከፍ ሊያደርገው ይችላል ብለዋል ዋና ኢንስፔክተሩ።
የአረርቲ ሆስፒታል ተወካይ ኀላፊ ስዩም አልታዬ ከቀይ መስቀል ጋር በመተባበር ለተጎጂዎች የሕክምና ድጋፍ እየተሰጡ እንደኾነም ገልጸዋል።
ከሆስፒታሉ አቅም በላይ የኾነ ጉዳት የደረሰባቸው ስድስት ታካሚዎችን ሪፈር እንዳሉ የገለጹት ተወካይ ኀላፊው ይህ መረጃ እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስ ከ70 በላይ ሰዎች የህክምና ድጋፍ እየተሰጣቸው መኾኑን ተናግረዋል።
ጉዳታቸው ቀለል ያሉትን ደግሞ በአካባቢው ወደሚገኙ የጤና ተቋማት እያዘዋወሩ መኾኑን ገልጸዋል።
የደረሰው አደጋ ድንገተኛ እና ሰፊ በመኾኑ መሰል የጤና ተቋማት ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።
ዘጋቢ:- ለዓለም ለይኩን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!