የኢትዮጵያ ሰርኩላር ኢኮኖሚ የፅዱ ኢትዮጵያን ዕሳቤ ለማሳካት ወሳኝ ሚና ይጫወታል።

3
አዲስ አበባ: መስከረም 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) “የኢትዮጵያ ሰርኩላር ኢኮኖሚ 2025” የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ለሊሴ ነሜ የኢትዮጵያ ሰርኩላር ኢኮኖሚ የደረቅ ቆሻሻ አያያዝ እና አወጋገድ ሥርዓትን በማዘመን የፅዱ ኢትዮጵያን ዕሳቤ ለማሳካት ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል።
ሀገሪቱ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ዕቅድን በመተግበር ፅዱ እና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማውረስ በብርቱ እየሠራች መኾኑን ገልጸዋል። የኢትዮጵያን ሰርኩላር ኢኮኖሚ ቆሻሻን መልሶ በመጠቀም ረገድ በሚሠራው ሥራ በርካታ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንደሚያስገኝ አስረድተዋል።
ሰርኩላር ኢኮኖሚ ብክለትን እና ብክነትን በመቀነስ የዘላቂ የአካባቢ ሃብት አጠቃቀም መርህን በተሟላ መልኩ በመተግበር የካርበን ልቀትን በመቀነስ አካባቢ ላይ የሚደርስን ጫና ማስቀረት ያስችላል። ይህም ለፅዱ እና ለበለጸገች ኢትዮጵያ ዕውን መኾን ቁልፍ ነው ተብሏል።
የኢትዮጵያ ሰርኩላር ኢኮኖሚ ቆሻሻን መልሶ መጠቀምን በማበረታታት ከኢኮኖሚያዊ ጥገኝነት ለማላቀቅ የሚያስችል መኾኑንም ጠቁመዋል።
በተለይም ፕላስቲክን ለማስወገድ በሚደረገው ሥራ የፈጠራ ክህሎትን ማዳበር እና ጤናማ ውድድር መፍጠር ለአረንጓዴ የሥራ ዕድል ፈጠራ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክትም አስረድተዋል።
ሰርኩላር ኢኮኖሚ ሃብትን በአግባቡ ለመጠቀም፣ አካባቢን ለመጠበቅ፣ ለኢኮኖሚ ዕድገት እና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ምርቶችን ለማቅረብ፣ ለአረንጓዴ ሥራ ፈጠራ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር አብራርተዋል።
ይህ ሀገራዊ ዕቅድ ፈጠራን ከማበረታታት ባለፈ፣ በራስ አቅም እና ግብዓት ምርቶችን በማምረት የሥራ ዕድል በመፍጠር ትልቅ ሚና አለው።
ዘላቂ የአካባቢ ጥበቃ ሥራ በመሥራት የተፈጥሮ ሃብትን የመጠበቅ እና ፅዱ ኢትዮጵያን የመፍጠር፣ ለቀጣዩ ትውልድ ንፁህ እና ፅዱ አካባቢን ለማስረከብ የጎላ ሚና እንደሚጫወት አመላክተዋል
ዘጋቢ፦ ሰለሞን አሰፌ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleጉባኤው ዳኞች እና የጉባኤ ተሿሚዎች የጋራ ዓላማ እና የጋራ ግብ እንዲኖራቸው ያደርጋል።
Next articleአረጋውያንን መንከባከብ ሀገርን መንከባከብ ነው።