ጉባኤው ዳኞች እና የጉባኤ ተሿሚዎች የጋራ ዓላማ እና የጋራ ግብ እንዲኖራቸው ያደርጋል።

4
ባሕር ዳር: መስከረም 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የዳኞች ጉባኤ እየተካሄደ ነው።
ጉባኤው ዳኞች ለጋራ ራዕይ እና ለጋራ መዳረሻ የጋራ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ያደርጋል ተብሏል።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ልዩ አማካሪ ወርቁ ያዜ የዳኞች ጉባኤ በክልሉ ከአሁን ቀደም ያልነበረ ታላቅ ጉባኤ መኾኑን ገልጸዋል።
“የጋራ ርዕይ ለጠንካራ የዳኝነት ሥርዓት” በሚል መሪ መልዕክት የሚካሄደው ጉባኤው ዳኞች እና የጉባኤ ተሿሚዎች የጋራ ዓላማ እና የጋራ ግብ እንዲኖራቸው ያደርጋል ነው ያሉት።
ጉባኤው የጋራ ዕይታ እና የጋራ ግንዛቤ እንዲኖር እንደሚያስችልም ተናግረዋል። የጋራ አመለካከት እና የጋራ ግንዛቤ ሲኖር ውጤታማ ሥራ መሥራት እንደሚቻልም ነው የገለጹት።
ከአማራ ክልል የ25 ዓመቱ የአሻጋሪ ዕድገት እና የዘላቂ ልማት ዕቅድ የፍርድ ቤቱ የራሱ ድርሻ አለው ያሉት ልዩ አማካሪው በ25 ዓመታት ውስጥ ምን ማሳካት እንደሚገባ የጋራ ግንዛቤ እንዲኖር የሚያስችል ጉባኤ ነው ብለዋል።
ፍርድ ቤት የሕዝብ አገልጋይ መኾኑንም ተናግረዋል። ዳኞች ሕዝብን በታማኝነት፣ በቅልጥፍና እና ወጭ ቆጣቢ በኾነ መንገድ ማገልገል እንደሚገባቸውም አንስተዋል። ፍትሕ አጣሁ ያሉ ወገኖች በፍጥነት ፍትሕ የማግኘት መብታቸው ሊረጋገጥ ይገባልም ነው ያሉት።
የዳኝነት ሥርዓቱ ዋነኛ ዓላማ ሕዝብን በፍትሕ ማርካት ነው ያሉት ልዩ አማካሪው ሕዝቡ ፍርድ ቤቶች ላይ ፍትሕ አገኛለሁ ብሎ ተማምኖ እንዲመጣ ማድረግ ከዳኞች እንደሚጠበቅም ተናግረዋል።
ጉባኤው የኅብረተሰቡን የፍትሕ ችግር ለመቅረፍ እና ኅብረተሰቡም በፍርድ ቤቶች ላይ አመኔታ ኖሮት እንዲመጣ ያስችላል ነው ያሉት።
ዳኞች አገልግሎት ለመስጠት የሚታመኑ መኾን አለባቸው ብለዋል። ኅብረተሰቡም ፈርጆ የሚቀርብ ሳይኾን ዕውነተኛ ፍትሕን አገኛለሁ ብሎ መምጣት አለበት ነው ያሉት።
ፍርድ ከተሰጠ በኋላ ሳይኾን ገና ጉዳዩን ይዞ ሲመጣ ዕውነተኛ ፍትሕ አገኛለሁ ብሎ ተማምኖ እንዲመጣ ኅብረተሰቡ ላይ መሥራት ይጠበቃል ብለዋል።
ማኅበረሰቡ ወደ ፍርድ ቤቶች ከመምጣቱ አስቀድሞ የቆዩ የሽምግልና እና የእርቅ እሴቶቹን መጠቀም አለበት ነው ያሉት። በሽምግልና የማይጨረስ ሲኾን ደግሞ ፍትሕን የሚሰጥ ተቋም አለ ብሎ በመተማመን እንዲመጣ እንደሚፈልጉም ጠቁመዋል።
ፍርድ ቤቶች ነጻ እና ገለልተኛ ኾነው እንደሚሠሩም ተናግረዋል። ኅብረተሰቡ የዳኝነት ሥርዓቱን የሚጎዱ አካሄዶችን መታገል እንደሚገባውም አንስተዋል። ፍርድ ቤቶች የመጨረሻ የመብት ማስከበሪያዎች ናቸውም ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየሕዝብን መብት እና ጥቅም የሚጎዱ ጉዳዮችን ለመፍታት ትኩረት ተሠጥቶ እየተሠራ ነው።
Next articleየኢትዮጵያ ሰርኩላር ኢኮኖሚ የፅዱ ኢትዮጵያን ዕሳቤ ለማሳካት ወሳኝ ሚና ይጫወታል።