
ባሕር ዳር: መስከረም 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ከሰሜን ጎጃም ዞን ፍትሕ መምሪያ እና በሥሩ ከሚገኙ የፍትሕ ጽሕፈት ቤቶች ኀላፊዎች እና ዐቃቤያን ሕግ ጋር በ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ውይይት እያካሄደ ነው። በ2017 በጀት ዓመት የተሠሩ ሥራዎችም ቀርበዋል።
የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኀላፊ ብርሃኑ ጎሽም እንዳሉት ፈጣን፣ ውጤታማ፣ ተደራሽ እና በሕዝብ ዘንድ ታማኝነት ያለው የፍትሕ ሥርዓት በመገንባት የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ የፍትሕ ተቋማት ተግባር ነው።
በ2017 በጀት ዓመት ለፍትሕ ሥርዓቱ በተሰጠው ትኩረት የወንጀል እና የፍትሐብሔር መዝገቦችን የመወሰን ቅልጥፍና እና ተከራክሮ የማሸነፍ ውጤታማነት እስከ 97 በመቶ ማድረስ መቻሉን ገልጸዋል።
በክልሉ ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ በወንጀል የተመዘበረ የመንግሥት ሃብት የማስመለስ ሥራ ተሠርቷል ነው ያሉት። በወንጀል ከተቀጡ ሰዎች ላይ ደግሞ ከ17 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ቅጣት ማስመለስ መቻሉን ገልጸዋል።
ከፖሊስ ጋር በቅንጅት በተሠራው ሥራ ከ16 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የከተማ መሬት ከወረራ ማስመለስ መቻሉንም ተናግረዋል።
የኅብረተሰቡን ተሳትፎ ለማሳደግ 68 ለወንጀል ጠቋሚዎች እና ምስክሮች የሕግ ከለላ ተሰጥቷል ብለዋል። የፍትሕ ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱን ሊያሳኩ የሚችሉ 55 የተለያዩ ሕጎችን የማዘጋጀት እና የማጽደቅ ሥራ እንደተሠራም አስገንዝበዋል።
የፍትሕ እና የዳኝነት ሥርዓቱን ለማዘመን እና ለማሻሻል የሚያስችል የ25 ዓመት የአሻጋሪ ዕድገት እና የዘላቂ ልማት ፍኖተ ካርታ የተቀዳ የ5 ዓመት ስትራቴጅክ ዕቅድ እና የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ታቅዶ ተግባራዊ እየኾነ መኾኑንም ነው የገለጹት።
በዚህ ደግሞ የመንግሥት እና የሕዝብ መብት እና ጥቅምን የሚጎዱ የሙስና ወንጀሎች፣ ከኢንቨስትመንት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች፣ የከተማ መሬት ወረራ እና በግዥ ሥርዓቱ ላይ የሚታዩ ብልሹ አሠራሮች ትኩረት የሚሠጣቸው ጉዳዮች መኾናቸውንም አብራርተዋል።
የመምህራን ቦታ ካሳ ክርክር፣ ከመንግሥት ግንባታ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች፣ የሰብዊ መብት ጥበቃ፣ የወንጀል የገንዘብ ቅጣትን እና በወንጀል ምክንያት የተመዘበረ ሃብትን ማስመለስ በዕቅድ የተለዩ ጉዳዮች መኾናቸውን አንስተዋል።
የፍትሕ ባለሙያው የፍትሕ ሥርዓትን ለመገንባት በሚደረገው ሂደት የራሱን ድርሻ እንዲወጣም አሳስበዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!