የባሕር በር ጥያቄ ለኢትዮጵያውያን የህልውና ጉዳይ ነው።

4
ገንዳ ውኃ፡ መስከረም 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ተገቢ በመኾኑ ሃሳቡን እንደሚደግፉት በምዕራብ ጎንደር ዞን የገንዳ ውኃ ከተማ ነዋሪዎች ለአሚኮ ተናግረዋል።
በታላቁ የሕዳሴ ግድብ የታየው አንድነት፣ ትብብር እና ጽናት በባሕር በሩ ላይም መድገም እንደሚያስፈልግ ነዋሪዎቹ ገልጸዋል። ለኢትዮጵያውያን የባሕር በር የሕልውና ጉዳይ መኾኑንም አስረድተዋል።
የባሕር በር በኢኮኖሚው ዘርፍ የንግዱን እንቅስቃሴ ለማሻሻል እና በቀላሉ የወጭ እና ገቢ ንግድ ለማድረግ ጠቀሚታው የጎላ መኾኑንም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።
ከሌሎች አጎራባች እና የዓለም ሀገራት ጋር ኢትዮጵያ ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር እና የሥራ ዕድል ለመፍጠርም የባሕር በር ከፍተኛ አበርክቶ እንዳለው ተሳታፊዎች አብራርተዋል።
በገንዳ ውኃ ከተማ አሥተዳደር የመተማ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ እና መሠናዶ ትምህርት ቤት የታሪክ መምህር እንዳልካቸው ደማስ ኢትዮጵያ ቀደምት ከ30 ዓመታት በፊት የባሕር በር እንደነበራት ታሪክ እንደሚያስረዳ ጠቅሰው አሁን ላይ የባሕር በር ለማግኘት እና የቀደመውን ለመመለስ የሚደረገው ጥረት ተገቢ መኾኑን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ የራስ የነበረን የማስመለስ ጉዳይ መኾኑን መምህር እንዳልካቸው ጠቁመው ዓለም አቀፍ መርሆዎችን የተከተለ ተገቢ የመብት ጥያቄ መኾኑንም አንስተዋል።
እንደ ታሪክ መምህሩ ገለጻ የባሕር በርን ለማስመለስ በሰላም እና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ መኾን እንዳለበት ጠቁመዋል። በተባበረ መንገድ እና በአንድነት እንደ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ዕውን ማድረግ እንደሚገባም ገልጸዋል።
የባሕር በር ጥያቄ ኢትዮጵያ ለሌሎች ሀገራት ለወደብ የምትከፍለውን ታክስ የሚያስቀር እና ሉዓላዊነትን በማስከበር በቀጣናው ተደማጭነቷን ለማጉላት እንደሚያግዛት የታሪክ መምህሩ ተናግረዋል።
የገንዳ ውኃ ከተማ አሥተዳደር ትምህር ጽሕፈት ቤት ምክትል ኀላፊ ኤፍሬም መኩሪያው የባሕር በር ጥያቄ ለሀገሪቱ የሚሰጠውን ጥቅም በመገንዘብ ሁሉም አካላት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ መወጣት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
ምሁራን በታሪክ እና በጥናት ላይ ተመስርተው ስለኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ እያ አስፈላጊነት ለተተኪው ትውልድ ማስተማር እና ዕውቅና በመፍጠር ቀዳሚ ተግባር ማድረግ አለባቸውም ብለዋል።
በተወሰኑ ሰዎች የፖለቲካ ሽኩቻ ያጣነውን የባሕር በር በአንድነት እና በመተባበረ እንዲመለስ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ጉዳይ ዕውን ከኾነ የባሕር ትራንስፖርት ዘርፉን እንደሚያነቃቃውም አቶ ኤፍሬም ተናግረዋል። ቀደም ሲል የነበረውን የባሕር ኀይል ለመገንባት እና ለማቋቋምም እንደሚያስችል አስገንዝበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article”ሙስናን ለመታገል ቁርጠኛ መኾን አለብን” አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ
Next articleየሕዝብን መብት እና ጥቅም የሚጎዱ ጉዳዮችን ለመፍታት ትኩረት ተሠጥቶ እየተሠራ ነው።