አረጋውያንን መርዳት የዜጎች ግብረ ገባዊ ግዴታ መኾን አለበት።

4
ባሕር ዳር፡ መስከረም 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ጊዜው 2010 ዓ.ም ነው፤ ጎንደር ከተማ ላይ ወጣቱ ከሥራ ወደ ቤቱ ያቀናል፤ ይህ ወጣት ግን በመንገድ ላይ ባየው አንድ ነገር ላይ ዐይኑ ያርፋል። አንድ በዕድሜ ጠና ያሉ አረጋዊ መንገድ ላይ ወድቀዋል።
ወጣቱ የወላጅ አባቱን ያህል የአረጋዊው ሰው መንገድ ላይ መውደቅ እና የነበሩበት ሁኔታ ድንገት ሳያስበው ወደ አዛውንቱ ሰው ተጠግቶ እንዲያያቸው አስገደደው። በወቅቱ ሰዎች የዕለት ተግባራቸውን ከመከወን ውጭ ለእነዚህ አባት ትኩረት የሰጣቸው አልነበረም።
ይህ ወጣት ግን ተጠግቶ በትኩረት ተመለከታቸው አቃንቶ ደግፎ ይዞ በለኾሳስ ከሚያወጡት ድምጽ ሁኔታቸውን ጠየቀ። እኝህ አረጋዊ ሀገራቸውን በተለያየ ሁኔታ ያገለገሉ ቢኾኑም ትኩረት አጥተው ጧሪ እና ቀባሪ አልባ ኾነው አገኛቸው።
ወጣቱ ትቷቸው ሊሄድ አልደፈረም። ይልቁንም አዝሎ ወደ ሕክምና አድርሶ ሐኪሞች እንዲያዩአቸው አደረገ። ከዛም ሌሎች ሁለት እንደሱ ደጋግ የኾኑ ወጣቶች የሚያደርገውን ነገር ደግፈው ከጎኑ ቆሙ። አዛውንቱንም ገላቸውን አጥበው ጸጉራቸውን ላጩ።
ቀጣዩ አሁን እነዚህን አዛውንት የት እናድርጋቸው የሚለው አሳሳቢ ኾነ። በእርግጥ በወቅቱ ከእነዚህ ደጋግ ወጣቶች ዐይን የገቡት እኒህ አዛውንት ይሁኑ እንጅ በርካታ መንገድ ላይ የወደቁ አረጋዊያን እንዳሉ ተረድተዋል። በመኾኑም እነዚህን ረዳት የሌላቸውን አረጋውያን እና ሕጻናትን መርዳት የሚችሉበትን ሁኔታ መላ ዘየዱ፤ ካለን ብናካፍል የበጎ አድራጎት ማዕከልም ዕውን ኾነ።
የማዕከሉ ሥራ አሥኪያጅ ዳዊት አየነው በወቅቱ ማዕከሉን ለመመሥረት ብዙ ውጣ ውረድ ስለመታለፉ ያብራራል። ብዙ የተደከመለት ተቋም አሁን ላይ ሀገር እና ወገን የሚኮራበት ተቋም መኾን ስለመቻሉም ነው የሚገልጸው።
አረጋዊያን እንዳሁኑ ጉልበታቸው ሳይዝል ለሀገር መኩሪያ ኾነው ሀገር ያቀኑ ስለመኾናቸው ገልጿል። በሠሩት ልክ ክብር እንደሚገባቸውም ነው የገለጸው።
የካለን ብናካፍል የሕጻናት፣ አረጋውያን እና ሕሙማን መርጃ ማዕከል አሥተባባሪ ፍቅረ ማርያም ሥጦታው እንደነገረን ማዕከሉ ከተመሠረተ ገና ሰባት ዓመቱ ነው። በቆይታውም ብዙ እየሠራ የሚገኝ ማዕከል እንደኾነ ነው የገለጹት።
ማዕከሉ በተለይ በሜቄዶኒያ፣ በአማኑኤል ሆስፒታል እና በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል አካባቢ በጎ አድራጎትን በነጻ አገልግሎት መስጠት ጀምሮ ቀስ እያለ ጥር 2012 ዓ.ም ላይ ወደ አንድ ማዕከል ማምጣት መቻሉን ነው የተናገረው።
አሁን ላይ ጎንደር ከተማ ሁለት ቅርንጫፍ ከፍቶ አገልግሎት እየሰጠ ሲኾን ከአረጋውያን እስከተለያዩ ጉዳቶች የተዳረጉ ሰዎች አገልግሎት እንዲያገኙ እየተደረገ ስለመኾኑም አብራርተዋል።
አሥተባባሪው ተቋማቸው አሁን ላይ በውስጥ እና በቤታቸው ያሉ አረጋውያንን ጨምሮ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ነው ያብራራው። በተወሰኑ ሰዎች ግልጋሎት የጀመረው ማዕከሉ አሁን ላይ በውስጥ ብቻ 500 ሰዎችን እየረዳ ሲኾን ከእነዚህ ውስጥ 200 የሚኾኑት አረጋዊያን እንደኾኑ ጠቁሟል።
ሌሎች በውጭ 70 የሚያግዟቸው አረጋውያን እንዳሉም አብራርቷል። ይህ ነጻ አገልግሎትም በ20 ነጻ የበጎ አገልግሎት ሰጭ ሰዎች እየተመራ እንደሚገኝም ነው ያስገነዘበው። ጎንደር ዩኒቨርሲቲ እና ኢትዮ ቴሌኮም ድጋፍ ከማድረጋቸው በተጨማሪ ግለሰቦች እና የጎንደር ከተማ አሥተዳደር አስፈላጊውን የቦታ እና የባለሙያ ድጋፍ እያደረጉ እንደኾነም ጠቁሟል።
የኪነ ጥበብ ሰዎች እና ታዋቂ ሰዎች አሁን ላይ አረጋውያን እንዲታገዙ ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኙም ነው ያስገነዘበው። ለካለን ብናካፍል እስካሁን ድጋፍ ላደረጉ ሁሉ አመስግኗል። ማዕክሉ እስካሁን ለሀገራቸው ሲያገለግሉ ቆይተው አሁን አጋዥ ላጡ ሰዎች አስፈላጊውን እገዛ ለማድረግ ቋሚ ገቢ የሚያገኝበትን ዕድል መፍጠር እንደሚገባም አስረድቷል።
በተለይም በድጋፍ የሚያገኘው ከበጎ አድራጊዎች በመኾኑ ትንሽ ኮሽ ባለ ቁጥር ረጅዎች የሚርቁበት ሁኔታ በመኖሩ ቋሚ ገቢ ማስገኛ ላይ መሥራት እንዲቻል ሁሉም ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቋል።
በጎንደር ከተማ ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ሙሉቀን ጌታሁን ከተማ አሥተዳደሩ ዓለም አቀፍ የአረጋውያን ቀንን ሲያከብር ባሉት ስድስት ክፍለ ከተሞች ለሀገር ባለውለታ የኾኑትን አረጋውያንን ያለባቸውን ችግር በመለየት እና ድጋፍ በማድረግ እያከበረ ይገኛል ብለዋል።
በተለይ እስካሁን ከተደረገው ድጋፍ በተጨማሪ በዚህ በዓል ላይ ከየክፍለ ከተሞቹ የተውጣጡ 50 አረጋውያን አስፈላጊውን ቁሳቁስ ለመደገፍ እየሠሩ እንደሚገኙም ነው የተናገሩት።
መምሪያው አረጋውያንን እያገዙ ያሉ ልክ እንደ ካለን ብናካፍል ያሉትን ለመደገፍ ሥራ መሥራቱን ጠቁመዋል። በተለይም ከቴሌ ጋር በመገናኘት በመልዕክት ገቢ እንዲያገኙ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም አብራርተዋል።
አረጋውያን በሥርዓተ መንግሥት ውስጥ የራሳቸውን አሻራ እያሳረፉ የመጡ በመኾኑ ሁሉም አስፈላጊውን ድጋፍ አድርጎ የነገ ሀገርን ማቆም ይገባል ብለዋል።
አረጋዊያን በተለያዩ አገልግሎቶች ላይ ወገናቸውን ሲጠቅሙ የቆዩ በመኾናቸው እነዚህ ሰዎች ከመረዳት ወጥተው የራሳቸው ቋሚ ገቢ እንዲኖራቸው የአረጋውያን ሕንጻ ለመገንበት ጥረት እየተደረገ በመኾኑ ሁሉም የሚችለውን በማድረግ እንዲያግዝም ነው ያሳሰቡት።
ለሀገር ማገልገል ክብር እንደኾነ የሚገለጸው በአሁኑ የአረጋውያን እገዛ በመኾኑ አረጋውያኑ ሰባዊ አገልግሎት ላይ የሚገባቸውን እንዲያገኙ ማድረግ ከሁሉም ይጠበቃል ነው ያሉት።
በአማራ ክሌል የሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ምጥን ብርሃኑ ዓለም አቀፍ የአረጋውያን ቀን መስከረም 21 ቀን ሲከበር ለአረጋውያን ደኅንነቶች እና መብት መጠበቅ ሁለንተናዊ ኀላፊነት እንወጣ በሚል መሪ መልዕክት እንደኾነ ጠቁመዋል።
ቢሮው ከትልልቅ ተቋማት እስከ ታች መዋቅር ድረስ የአረጋውያንን አስተዋጽኦ በሚያሳይ መንገድ እንደሚያከብሩትም ነው የጠቆሙት። በተለይም አረጋውያን ተጠቃሚ የሚኾኑባቸውን ምቹ ሁኔታ በመፍጠር እና የወጡ ሕጎች እንዲተገበሩ ግንዛቤ በመፍጠር እንደሚከበር ነው ያስረዱት።
የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊዋ እንዳሉት አረጋውያን በሀገሪቱ በተለያዩ መስኮች ሕዝብን ሲያገለግሉ የነበሩ እና ሀገር ከነሙሉ ክብሯ ሉዓላዊነቷ ተጠብቆ ለተከታዩ ትውልድ ያሻገሩ በመኾናቸው አስተዋጿቸው ታሳቢ ተደርጎ መብት እና ደኅንነታቸው እንዲጠበቅ ማድረግ ዋና ቁልፍ ጉዳይ ነው ብለዋል።
አረጋውያን አሁን ባሉበት ደረጃም ከመታገዝ ባለፈ ጥሩ ዜጋ እና ሀገሩን የሚወድ ለሰላም የሚተጋ ዜጋ በመፍጠር በኩል የሚጠበቅባቸው በመኾኑ ይህን እንዲሠሩ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ይገባል ነው ያሉት።
አሁን ካለው ሁኔታ አንጻር ባሉበት ዕድሜ ክልል ኾነው መርህ ላይ የቆመ ሥነ ምግባር ያለው ብቁ እና ጤነኛ ማኅበረሰብ እንዲፈጠር የማስተማር ኀላፊነታቸውን መወጣት እንደሚገባቸውም ነው ያሳሰቡት።
ክልሉ በዚህ ዓመት አንድ ተቋም ለአንድ አረጋዊ በሚል እየሠራ ሲኾን እያንዳንዱ ተቋም መሥራት የማይችሉትን ሊታገዙ የሚችሉበትን ተቋም ልክ እንደ ካለን ብናካፍል አይነት ተቋማትን በመፍጠር ማገዝ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
መሥራት የሚችሉትን ደግሞ ሠርተው የሚጠቀሙበት የገቢ ማስገኛ እንዲፈጠር ጥረት እንዲደረግ እየተሠራ ነው ብለዋል። በክልል ደረጃም ምሳሌ የሚኾን የአረጋውያን የገቢ ማስገኛ ሕንጻ መሠረቱ ተጠቃሽ እንደኾነም ተናግረዋል። አረጋውያንን ለማገዝ የሚመጣን አካል ቢሮው አብሮ እንደሚሠራም ነው የተናገሩት።
የተደራጁ ማዕከሎች እየሰጡት ያለው አገልግሎት ደረጃውን ስለመጠበቁ ቁጥጥር እንደሚደረግም አስገንዝበዋል። የአረጋውያን ጉዳይ የአንድ ተቋም ብቻ ኀላፊነት ባለመኾኑ ማዕከላቱም አስፈላጊውን እገዛ ከተለያየ አቅጣጫ እንዲያገኙ አብሮ የመሥት ሥራ እንደሚሠራም ነው ያስገነዘቡት።
ኢትዮጵያውያን በሞት፣ በሕመም፣ በድንገተኛ አደጋ እና ሕይወትን ከሞት ለመታደግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ የቆየ የመረዳዳት ግብረ ገባዊ እሴትን ያዳበሩ ሕዝቦች ናቸው።
ይሁን እንጂ መረዳዳቱ ዘላቂ ዕድገት በሚያመጡ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ባለመኾኑ ለችግሮች መወሳሰብ እና መግዘፍ ምክንያት እንደኾነ ስለግብረ ገብነት የጻፉት ምሑር ጠና ደዎ(ዶ.ር) “ሰው ግብረ ገብና ሥነ ምግባር የዘመናችን ቁልፍ ጉዳዮች” በሚለው መጽሐፋቸው ገልጸውታል።
“ለአረጋውያን ወገኖች በየትኛውም ሥፍራ እና ጊዜ ማንኛውንም ማኅበራዊ አገልግሎት መሥጠት እና መርዳት የዜጎች ግብረ ገባዊ ግዴታ እንደኾነ” የሚገልጹት ምሑሩ ሁሉም ዜጋ የትናንቱን አጥብቆ በመያዝ የነገውን መገንባት እንዳለበት ነው በመጽሐፋቸው አንስተዋል።
ዘጋቢ፦ ምሥጋናው ብርሃኔ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleየዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ምክር ቤት ጉባኤውን እያካሄደ ነው።
Next article”ሙስናን ለመታገል ቁርጠኛ መኾን አለብን” አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ