“ደጋጎቹ የሚናፍቁሽ፤ ብርሃን ያረፈብሽ”

12
መስከረም፡ 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከፀሐይ የላቀው ብርሃን አርፎብሻል፤ የማይጠልቀው ጀንበር ታይቶብሻል፤ ዓለም የዳነበት መንበሩ አድርጎሻል፤ ቅዱሳኑ ከትመውብሻል፤ ደጋጎቹ ተጠልለውብሻል። መንፈስ ቅዱስ ረብቦብሻል።
አንቺ ከተመረጡት ተራራዎች መካከል ተመርጠሻል፤ አንቺ ከተባረኩት ተባርከሻል፤ አንቺ ከተቀደሱት ተቀድሰሻል።
አንቺ መላዕክት የከተሙብሽ አምባ ሆይ ከሁሉ ትልቂያለሽ፤ አንቺ መድኃኒት ያረፈብሽ ተራራ ሆይ አምላክ መርጦሻልና ከተራራዎች የበለጠ ትወደጃለሽ፤ አንቺ የብርሃን ከተማ ሆይ ለሚያምኑ ሁሉ ታበሪያለሽ፤ የጨለማውን ዘመን ትገፍፊያለሽ።
የተባረክሽ ነሽና መድኃኒት አረፈብሽ፤ የተባረክሽ ነሽና አስቀድመሽ ተመረጥሽ፤ የተቀደስሽ ነሽና የብርሃን ዙፋን ኾንሽ፤ የተቀደስሽ ነሽና ዓለማት የናፈቁትን ሁሉ ያዝሽ፤ የተመረጥሽ ነሽና እልፍ አዕላፋቱ ተጠለሉብሽ፤ መማጸኛ ነሽና ጽድቅን የወደዱ ተማጸኑብሽ፤ ያዘኑት መጽናኛ ነሽና የተከዙት ተጽናኑብሽ፤ የደከሙት በረቱብሽ፤ የታመሙት ተፈወሱብሽ፤ የተራቡት በሕይወት ሕብስት ጠገቡብሽ፤ የተጠሙት በሕይወት ውኃ ረኩብሽ፤ የታረዙት በጸጋ ልብስ አጌጡብሽ።
በአንቺ ላይ ያረፈውን ዓለማት ይፈልጉታል፤ በአንቺ ላይ ያረፈውን ፍጥረታት ይሰግዱለታል፤ በአንቺ ያረፈውን ሞት እጅ ይነሳለታል። ጥልና ጥላቻ ይደነግጥለታል።
የተባረኩት አምባዎች ትዕዛዝ ይነገርባቸዋል፣ የተባረኩት አምባዎች ጽላት ይወርድባቸዋል፣ የተባረኩት አምባዎች መለኮት ይገለጥባቸዋል፣ የተባረኩት አምባዎች ትንቢት ይነገርባቸዋል፣ የተባረኩት አምባዎች መስቀል ይቀመጥባቸዋል፣ የማይጠፋ ብርሃን ይበራባቸዋል፣ የተባረኩት አምባዎች ደብር ይደበርባቸዋል፣ ገዳም ይገደምባቸዋል፣ መጻሕፍት ይጻፉባቸዋል፣ የተቀደሱ ቅርሶች ይኖሩባቸዋል፡፡ በተባረኩት አምባዎች ጻድቃን ይጠለላሉ፣ ቅዱሳን ይሠበሠባሉ፣ ደጋጎች ይኖራሉ፡፡
በተባረኩት አምባዎች ሰላም ይሰበክባቸዋል፤ በተባረኩት አምባዎች ፍቅር ይነገርባቸዋል፤ ድኅነት ይደረግባቸዋል፤ ቃል ኪዳን ይፈጸምባቸዋል።
በተባረኩት አምባዎች የሚኖሩት ደጋጎች ለምድር በረከት ይለምናሉ፣ ፍዳና ስቃይ እንዲርቅ ይማጸናሉ፣ ከፈጣሪ ጋር በሰርክ በጸሎት ይገናኛሉ፣ ስጋቸውን አስርበው፣ ነብሳቸውን አጥግበው ይኖራሉ፡፡ ፈጣሪም የደጋጎችን ልመና ይሰማቸዋል፣ የለመኑትን ይሰጣቸዋል፣ ምድርን ይባርክላቸዋል፡፡ ግሸን ከተባረኩት የተባረከች፣ ከተቀደሱት የተቀደሰች ናት።
መጽሐፈ ጤፉት ግሸን ደብረ ከርቤ ቅድስት ማርያም እንደ ሌሎች ቦታዎች እጅ የተሰነዘረባት የመጥረቢያ ስለት የአረፈባት አይደለችም። በጥበበ እግዚአብሔር ብቻ ተቀርጻና ተገልጻ ለክርስቲያን ሁሉ የድኅነት መገኛ ሁና የተሰጠች ናት እንጂ ይላል።
የግሸን መገኛ ኢትዮጵያ ታይተው የማይጠገቡ ጌጦች፣ እጹብ የሚያሰኙ ቅርሶች፣ ምስጢራቸው የማይታወቅ ኪነ ሕንጻዎች በምድሯ ሞልተዋል፡፡ ስሟ ረቂቅ ነው፣ ክብሯ ልዩ ነው፣ በየገዳማቱ ምስጢራት ሞልተዋል፣ በየአድባራቱ የረቀቁ ጥበባት በርክተዋል፡፡ ብዙዎች ምስጢሯን ለማወቅ፣ ክብሯን ለማየት እግራቸው እስኪነቃ ወደ እርሷ ይጓዛሉ፣ በምድሯ እየተዘዋወሩ የከበሩ ሥፍራዎችን ያያሉ፣ ዓይተውም ይደነቃሉ፡፡
ጌታ ለሙሴ የሰጠውን ጽላቱን፣ በቀራንዮ ደሙ የተቀዳበትን ጽዋውን፣ በቀራንዮ የተሰቀለበትን መስቀሉን ሰጥቷታል፣ የተቀደሱት በእርሷ እንዲኖሩ መርጧታል፣ ከማዕት አሻግሯታል፣ ከስቃይና ከጨለማ ዘመን እያራቀ ጠብቋታል ኢትዮጵያን።
ሐይቆቿን በምስጢራት መላቸው፣ አምባዎቿን ባረካቸው ቀደሳቸው፣ የስሙ መጠሪያ፣ የክብሩ መመስከሪያ አደረጋቸው፡፡ በሲና ተራራ ተገለጠ፣ ትዕዛዛቱንም ለሙሴ ሰጠ፣ በታቦር ተራራ መለኮቱን ገለጠ፣ በግሸን ደብረ ከርቤ አምባሰል ተራራ መስቀሉን አስቀመጠ፣ ብርሃንንም ገለጠ።
ሀገራት ክርስቶስ የተሰቀለበትን መስቀል አብዝተው ፈለጉት፣ በምድራቸው ይኖር ዘንድ ወደዱ፤ ገሚሶች በጉልበት፣ ገሚሶች በብልሃት ይወስዱት ዘንድ ደከሙ፡፡ ለመስቀሉ መኖሪያ፣ ለስሙ መክበሪያ ስለመመረጣቸው ግን አላወቁም ነበር፡፡ የፈለገ ሁሉ አያገኝም። የተመኘ ሁሉ አይሳካለትም።
መስቀሉን የፈለጉት ሁሉ አላገኙትም፤ እንደ ተመኙትም በምድራቸው አላስቀመጡትም፤ አስቀድማ የተመረጠችው፣ በቅዱሳን የተከበበችው፣ ለምስክርነት የተቀመጠችው ኢትዮጵያ ግን መስቀሉ ያርፋባት ዘንድ ታደለች፡፡ እርሷ ከዘመናት በፊት መስቀሉ ይቀመጥባት ዘንድ የተዘጋጀ መስቀለኛ ተራራ የተፈጠረባት፣ በክብር የሚጠብቃት ሥፍራ ነበራት፡፡
በመጽሐፈ ጤፉት ላይ እንደተጻፈው ገና በግሸን ላይ ቤተክርስቲያን ከመታነጹ አስቀድሞ መላዕክት ቅዱስ መስቀሉ እስኪመጣ ድረስ ይጠብቋት ዘንድ ልዩ ቦታቸው አደረጓት። በቅድስናም ይጠብቋት ነበር።
ጊዜው ደረሰ። ከሀገረ እስራኤል ኢየሩሳሌም ሮማውያንን የሸሹ ሰዎች በየመን በሀገረ ናግራን ይኖሩ ነበር። በዚያ ምድር ዓለምን ንቀው የሰማዩን ርስት የሚሹ አንድ ጻዲቅ መነኩሴ ይኖሩ ነበር። እኒህ ጻድቅ ሰው የቀደመ ስማቸው ፍሊክስ የኋለኛው ስማቸው ደግሞ ፈቃደ ክርስቶስ ይባሉ ነበር።
ከቅዱሱ መናኝ ጋርም ሁለት ጽላቶች ነበሩ። የእግዚአብሔር አብና የቅድስት ድንግል ማርያም። ማርያምም ለቅዱሱ አባት በራዕይ ተገለጠችላቸው። ጽላቶቹን ይዘው የብርሃን ምሰሶ ተተክሎ ወደሚታይበት ሀገር ይሄዱ ዘንድ ነገረቻቸው። የተባሉትን አደረጉ።
አሥራ ሁለት መነኮሳትን አስከትለው በራዕይ ወደታዬቻቸው ምድር ገሰገሱ። አስቀድሞ ከተነገራቸው የብርሃን አምድ ከተተከለባት ምድር ደረሱ። የብርሃን አምድ ተመለከቱ፡፡ ፈቃደ ክርስቶስ የበሽሎን ወንዝ ተሻግረው ወደ ተራራው አቀኑ። ተራራው ከሁሉም ተራራዎች ይለያል። ወደላይ ሊወጡ ሲሉ ገደሉን ንብ ሠፍሮበት ነበር። የንቡ ብዛት የማሩ ሰፈፍ ያስደነቃቸው ቅዱስ መናኝ ይህስ አምባአሰል ነው አሉ። አሰል ማለት በአረበኛ ማር ነው። የማር አምባ ሲሉ አምባሰል አሏት። በመስቀል የተቀረጸ ምድር፣ የመናንያን፣ የባሕታዊያን የቅዱሳን፣ የበረከት ሀገር አምባሳል። ፈቃደ ክርስቶስ ወደ ተራራው የምታስወጣቸው አንዲት መንገድ አግኝተው ተከታዮቻቸውን አስከትለው ወደ ተራራው ወጡ። በዚያም መቃረቢያ ሠርተው እንደታዘዙት ሁለቱንም ጽላቶች በመስቀለኛው ተራራ ላይ አስቀመጧቸው።
ዘመን ዘመንን ተካ። ትውልድ እየተተካካ ዘመናት ቀጠሉ፡፡ በምድሯም አጼ ዘርዓያዕቆብ ከአባታቸው ከአጼ ዳዊት ዙፋንን ተቀብለው ነገሡ፡፡ እርሳቸውም ከአባታቸው ዙፋን ብቻ አልተቀበሉም፤ የከበረ ቃል ኪዳንንም ነበር እንጂ፡፡ እርሳቸውም መስቀሌን በመስቀለኛ ቦታ አኑር የሚል ቃል ተነግሯቸው ነበርና ከአባታቸው የተቀበሉትን መስቀል የት እንደሚያኖሩት ማንሰላሰል ጀመሩ፡፡ የተነገሩትን ምስጢራዊ ቃል ለመተግበር ግን ቀላል አልነበረም፡፡ መድከምን፣ በቅዱሳን መመራትን፣ ምስጢር መፍታትን ይጠይቃል እንጂ።
ንጉሡ ዘርዓያዕቆብ መስቀሉን በመስቀለኛ ያስቀምጡ ዘንድ ለካሕናቱ መስቀሉን አስይዘው የሚያሳርፉበትን ሥፍራ አሰሱ፡፡ በቀላል የሚገኝ አልነበረም፡፡ የጌታ ፈቃድ ይኾን ዘንድ ጸለዩ፡፡ ጌታም ጸሎታቸውን ሰማቸው፡፡ መስቀሉ የሚቀመጥበትን መስቀለኛ ሥፍራ አመላከታቸው፡፡ ያቺም መስቀለኛ ሥፍራ ግሸን ደብረ ከርቤ ናት።
መስቀሉን ለካህናቱ አሸክመው፣ በሊቃውንቱ እየተመሩ፣ በሠራዊቱ እየታጀቡ፣ በዕልልታ እና በሆታ ወደ መስቀለኛው ተራራ ወጡ። በተራራውም አስቀመጡት። ቤተ መቅደስም አሳነጹ። ቅዳሴ ቤቱም ከበረ።
ንጉሡ ቃል ኪዳናቸውን ፈጸሙ፡፡ ፈጣሪም ኢትዮጵያን ባረካት፣ ከፍ ከፍ አደረጋት። የዘላለዓለም ቃል ኪዳን ሰጣት። የማይለወጥ የማይናወጥ ቃል ኪዳን አሠረላት።
ግሸን ታላቋ ምድር በልዩ ልዩ ስያሜዎች ትጠራ ነበር። ደብረ ነጎድጓድ ፣ ደብረ እግዚአብሔር፣ ደብረ ነገሥት ትባል ነበር። ግማደ መስቀሉ ሲገባ ደግሞ ደብረ ከርቤ ተብላ ተጠራች። በቀደመው ዘመን በታላቋ ተራራ የካህናት እና የነገሥታቱ ልጆች ጥበበ ስጋን ከጥበበ ነብስ ጋር እያዋሃዱ ይማሩበት ነበር። ነገሥታቱ ይማጸኑበታል፣ በረከት ይለምኑባታል፣ ልጆቻቸውን የቤተመንግሥት ሥርዓት ያስተምሩባታል።
ግሸን የኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች መሠባሠቢያ አምባ ናት። የዓመት በዓሏ በሚታሰብበት ጊዜ ኢትዮጵያውያን ከመስቀሉ በረከት ለመቀበል ወደ መስቀለኛው ተራራ ይወጣሉ፣ ወደ ተቀደሰው ሥፍራ ያቀናሉ፡፡
መስቀል ኃይላችን ነው እያሉ፣ ወደ ተባረከችው አምባ ይገሰግሳሉ፡፡ ከግሸን ማርያም በረከት እና ረድኤት ለመቀበል በአጸዷ ሥር ይሠባሠባሉ። ለከፍታ ወደ ከፍተኛው ሥፍራ ይጓዛሉ፡፡ ከአራቱም ንፍቅ የሚነሱት አማኞች በአንድነት፣ በኅብረት፣ በሰላም እና በፍቅር ይጠለላሉ። በዚያች ስፍራ በረከት፣ ረድኤት፣ የጸና ሃይማኖት ተስፋ እና ፍቅር አለና፡፡
እነኾ የግሸን ዓመታዊ የንግሥ በዓል ደርሷል ቁጥራቸው የበዛ ክርስቲያኖች ባዘቶ የመሰለ ነጫጭ ልብሳቸውን በመስቀለኛ እየለበሱ ወደ መስቀለኛዋ ሥፍራ ወጥተዋል። ለበረከት እና ለረድኤት ተሠባሥበዋል። ለድኅነት በቅድስቲቷ ምድር ተገኝተዋል።
ሂዱ ወደ ዚያች ተራራ ውጡ የእግዚአብሔርን ድንቅ ነገር ትመለከታላችሁ። አስቀድማ የተመረጠችውን፣ በአምሳለ መስቀል የተፈጠረችውን ድንቅ ሥፍራ ታያላችሁ። በዚያች ሥፍራ አይተው የማይጠግቡት፤ መርምረው የማይደርሱበት የረቀቀ ምስጢር አለና።
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“ትምህርት ካቋረጥኩ ብዙ ጊዜ ስለሆነኝ ብዙ ነገሩን ረስቸዋለሁ” ትምህርት አቋርጣ የቆየች ተማሪ
Next articleየዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ምክር ቤት ጉባኤውን እያካሄደ ነው።