
መስከረም ፡ 21/2017ዓ.ም (አሚኮ) ትዕግስት አስሜ ትባላለች። ከሁለት ዓመት በፊት በደቡብ ጎንደር ዞን እስቴ ከተማ በሚገኝ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ እንደነበረች ነግራናለች። የ10ኛ ክፍል ትምህርቷን በማጠናቀቅም ወደ 11ኛ ክፍል ተዘዋውራ ነበር።
በአማራ ክልል በተፈጠረ የጸጥታ ችግር ምክንያት ግን በርካታ ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ተግባራቸውን መከወን ባለመቻላቸው ታዳጊዋ ትማርበት የነበረው ትምህርት ቤትም ተዘግቶ እንደነበር ገልጻልናለች። በዚህ ምክንያትም ትምህርቷን አቋርጣ ወደ ባሕር ዳር ከተማ እንደመጣች ጠቅሳልናለች። አሁን ላይ ኑሮዋን በባሕር ዳር ከተማ አድርጋ በጫማ ማስዋብ እና ማጠብ ሥራ ላይ መሰማራቷን ትናገራለች።
እንደሷ ትምህርታቸውን ያቋረጡ እና በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ያሉ ተማሪ ጓደኞች እንዳሏት ነግራናለች። ታዳጊዋ “ትምህርት ካቋረጥኩ ብዙ ጊዜ ስለኾነኝ ብዙ ነገሩን ረስቸዋለሁ” ነው ያለችን። ያለችበትም ሁኔታ ብዙ አስቸጋሪ ቀናትን እንድታልፍ እያደረጋት እንደኾነ ነው የጠቆመችው።
ጎበዝ ከሚባሉ ተማሪዎች ውሰጥ እንደነበረች የተናገረችው ተማሪ ትዕግስት እየሠራች መማር ብትፈልግም የሁኔታዎች አለመመቻቸት ለመማር እንዳላስቻላት ገልጻለች። የመሥሪያ ገንዘብ እና መሥሪያ ቦታ ቢመቻችላት ግን እየሠራች የመማር ፍላጎት እንዳላት ነግራናለች። እሷ እና እንደ እርሷ አይነት ታዳጊዎች ትምህርታቸውን ካቋረጡበት እንዲቀጥሉም የሚመለከታቸው አካላት እገዛ እንዲያደርጉ ጠይቃለች። የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የትምህርት ዕቅድ በጀት ክትትል እና ግምገማ ዳይሬክተር ዘመነ አበጀ በክልሉ ባለፉት ዓመታት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች በጸጥታ ችግር ምክንያት ከትምህርት ገበታ ማቋረጣቸውን ገልጸዋል።
ይህ ደግሞ ተማሪዎች በዕድሜያቸው መማር የሚገባቸውን ትምህርት ሳይማሩ በመቅረታቸው በሕይወታቸው ላይ ከፍተኛ የትምህርት ብክነት ችግር እንዲገጥማቸው አድርጓል ብለዋል። በትምህርት ዘርፉ ተወዳዳሪ እና ሀገርን የሚጠቅም ትውልድ ለማፍራት ሕጻናትም ኾኑ ወጣቶች አካላዊ እና አዕምሮአዊ ዕድገታቸውን ታሳቢ በማድረግ የተዘጋጀውን ሥርዓተ ትምህርት በወቅቱ መማር አለባቸው ነው ያሉት። የተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው መስተጓጎል እና ማቋረጥ ችግሩ ዘርፈ ብዙ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ የሥነ ልቦና ጫና በመፍጠር ለተለያዩ ማኅበራዊ ችግሮች መጋለጥንም እንደሚያስከትል አብራርተዋል።
አሁን ላይ በክልሉ እየኾኑ ያሉት ያለዕድሜ ጋብቻ፣ የጎዳና ሕይወት፣ ለሱስ መጋለጥ እና የመሳሰሉ ማኅበራዊ ቀውሶች የዚህ ውጤት እንደኾኑም ገልጸዋል። ትውልድን በትምህርት አንጾ ቤተሰብ እና ሀገር እንዲረከብ እንዲሁም እንዲጠቅም ማድረግ የሁሉም ዜጋ ግዴታ ነው ያሉት አቶ ዘመነ ይህን በማድረግ በኩል ግን ክፍተቶች እንዳሉ ተናግረዋል። ማንኛውም አካል ተማሪዎችን፣ መምህራንን እና ትምህርት ቤቶችን ለመማር ማስተማር ነጻ በማድረግ በተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መብቶች ኮንቬንሽን (UNCRC) የተደነገገውን አንቀጽ 28 (የሕጻናትን የትምህርት የመመማር መብት) ልናከብር ይገባልም ነው ያሉት። የተማሪዎችን የመማር ነጻነት በመንፈግ ትውልድ ከዚህ በላይ እንዲጎዳ መፍቀድ እንደማይገባ እና ሁሉም ባለድርሻ አካል ለችግሩ መፍትሔ መኾን እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!