
ባሕር ዳር፡ መስከረም 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የግሸን ደብረ ከርቤ አመታዊ የንግሥ በዓል ነገ መስከረም 21/2018 ዓ.ም ይከበራል፡፡
ምዕምናን እና ጎብኝዎችም ወደ ሥፍራው እያቀኑ ነው። ብዙዎቹ የመስቀሉን ክብር ለማሰብ በመስቀለኛው ተራራ ላይ ቀድመው ደርሰዋል።
ይህንን በዓል በተሳካ ሁኔታ ለማክበር የቅድመ ዝግጅት ሥራ መሠራቱን የግሸን ደብረ ከርቤ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ዋና አሥተዳዳሪ አባ ብስራተ ገብርኤል ክፍለ ማርያም ተናግረዋል፡፡
በዓመታዊ የንግሥ በዓሉ በርካታ ምዕምናን መገኘታቸው
አባ ብስራተ ገብርኤል ተናግረዋል።
የደብሩ አሥተዳደር ሰበካ ጉባኤ ማኅበረ ካህናቱ እና የአጥቢያው አማኞች በተለየ ሁኔታ የቅድመ ዝግጅት ሥራውን አጠናቅቀው ምዕምናን እና ጎብኝዎችን እየተቀበሉ መኾናቸውን ገልጸዋል።
የግሸን ደብረ ከርቤ ቅድስት ማርያም ዓመታዊ የንግሥ በዓል በድምቀት እንደሚከበርም አንስተዋል። በበዓሉ ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች እና ከውጭ የሚመጡ አማኞች እና ጎብኝዎች እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ለጎብኝዎቹ ምቹ የኾነ መስተንግዶ ለማቅረብ አስቀድሞ ሥራ መሥራቱን አንስተዋል።
ለንግሡ ለሚመጡ ምዕምናን የሚኾን ሰፊ ቦታ በመለየት እና በግንብ በማጠር ምቹ የኾነ ማረፊያ መዘጋጀቱንም ተናግረዋል፡፡
የግሸን ደብረ ከርቤ ቅድስት ድንግል ማርያም ዓመታዊ የንግሥ በዓል በአማራ ክልል የሀገር ውስጥ እና የውጭ ጎብኝዎችን ፍሰት በከፍተኛ ሁኔታ የሚጨምር በዓል ነው፡፡
ዘጋቢ፦ ሰናይት በየነ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን