
ደብረ ማርቆስ: መስከረም 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ባለፋት ሁለት ዓመታት በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ከትምህርት ውጭ የነበሩ ተማሪዎችን በ2018 ወደ ትምህርት ገበታቸው ለመመለስ ጥረት እያደረገ መኾኑን አስታውቋል።
በከተማ አሥተዳደሩ በተለያዩ የክፍል ደረጃዎች ከ33 ሺህ 700 በላይ ተማሪዎች በትምህርት ገበታ ላይ መኾናቸውንም ተገልጿል።
የትምህርት ቤቶችን ገጽታ በመገንባት እና ደረጃቸውን በማሻሻል በትምህርት ዘመኑ ከ41 ሺህ 20 በላይ ተማሪዎችን ለማስተማር ታቅዶ 33 ሺህ 728 ተማሪዎች ተመዝግበው በመማር ላይ እንደሚገኙ የተናገሩት የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ተሾመ ዋለ ናቸው።
ወደ ትምህርት ገበታቸው ያልተመለሱ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ ለማድረግ ከወላጆች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ ነው ብለዋል።
በ2017 ዓ.ም በከተማዋ በጸጥታ ችግር ውስጥ ኾነው የክልል እና ሀገር አቀፍ ፈተና የወሰዱ ተማሪዎች ጥሩ ውጤት አስመዝግበዋል ያሉት አቶ ተሾመ በቀጣይ “ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደትን በመፍጠር በሀገር አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ተማሪዎችን ለማፍራት ትኩረት ተሰጥቷል” ነው ያሉት።
በትምህርት እና በሥነ ምግባሩ የታነጸ ትውልድ ለመፍጠር ማኅበረሰቡ እና የሚመለከታቸው አጋር አካላት ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር በጋራ ሊሠሩ እንደሚገባም አቶ ተሾመ አሳስበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!