
ባሕር ዳር: መስከረም 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት “ነጻ እና ገለልተኛ ሲቪል ሰርቪስ ለላቀ አገልግሎት” በሚል መሪ መልዕክት ለሠራተኞቹ ሥልጠና ሰጥቷል።
የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ ምክር ቤቶች በሕገ መንግሥቱ የተሰጣቸውን ተልዕኮ የመፈጸም አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መመጣቱን ገልጸዋል። ነገር ግን የማኅበረሰቡን እርካታ ለማሟላት አሁንም ብዙ መሥራት ይጠበቃል ብለዋል።
የምክር ቤቶችን የመፈጸም እና የማሥፈጸም አቅም ለማሳደግም የአቅም ግንባታ ሥልጠና ሲሠጥ ቆይቷል፤ አሁንም እየተሠጠ ይገኛል ነው ያሉት።
ሠራተኞች የሚሰጡ ሥልጠናዎችን እንደ ግብዓት በመውሰድ በአመለካከት እና በሥነ ምግባር የተሟላ ስብዕና ተላብሰው ሕዝብን ማገልገል ይገባቸዋል ብለዋል።
በተቋሙ ከሚሰጡ ሥልጠናዎች ባለፈ በራሳቸው ጭምር አቅማቸውን በማሳደግ ሕዝብን በቅንነት ሊያገለግሉ እንደሚገባ አሳስበዋል። የግብረ ገብ እና የሥነ ምግባር እሴትን ተላብሶ ሕዝብን ማገልገል እንደሚገባም አመላክተዋል።
ዘጋቢ:- ዳግማዊ ተሠራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!