አረጋውያን የሀገርን እሴት፣ ባሕል እና ወግ ለትውልድ ያቆዩ ባለውለታ ናቸው።

10
ባሕር ዳር: መስከረም 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ‎ዓለም አቀፍ የአረጋውያን ቀን በየዓመቱ መስከረም 21 ቀን ይከበራል፡፡ የዘንድሮው የአረጋውያን ቀን በዓለም ለ35ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ለ34ኛ ጊዜ ይከበራል፡፡
በዓሉን በተመለከተ አማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ እና የአማራ ክልል አረጋውያን ማኅበር መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
‎‎የአማራ ክልል አረጋውያን ማኅበር ምክትል ሰብሳቢ አምሳሉ መዓዛው የሞራል፣ የደግነት፣ የአብሮነት፣ የታታሪነት፣ የነጻነት ልዕልና እና የጥበብ ባለቤት የኾናችሁ አረጋውያን የእንኳን አደረሳችሁ ብለዋል።
‎‎2018 ዓ.ም ሰላም እና መረጋጋት የሰፈነበት፣ የአረጋውያን ድህነት እና ተጋላጭነት የሚቀንስበት፣ በድህነት ውስጥ የሚገኙ አረጋውያን ወደ ከፋ ድህነት እንዳይገቡ የምንከላከልበት እንዲኾን እንሠራለን ነው ያሉት።
ፍትሐዊ የሃብት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ጥረት የሚደረግበት ዘመን እንዲኾንም ኀላፊነታችን እንወጣለን ነው ያሉት፡፡
‎‎የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኀላፊ ንጹሕ ሽፈራው ‎‎ቀኑ “ለአረጋውያን ደኅንነት መጠበቅ ሁለንተናዊ ኀላፊነታችን እንወጣ” በሚል መሪ መልዕክት ይከበራል ብለዋል፡፡
‎‎በዓሉ የሚከበረው የሀገር ባለውለታ የኾኑ አረጋውያንን ለማክበር፣ ለመዘከር እና ለእነሱ ያለንን ፍቅር እና አክብሮት መግለጽ አስፈላጊ በመኾኑ ነው ብለዋል፡፡ “አረጋውያን የሀገር ባለውለታ ናቸው” ያሉት ምክትል ኀላፊዋ የሀገርን እሴት፣ ባሕል፣ ወግ ይዘው ለትውልድ ያቆዩ ባለውለታ በመኾናቸው በዚህ ቀን እነሱን ማሰብ ተገቢ መኾኑን ገልጸዋል፡፡
‎‎አረጋውያን በጤና መታወክ፣ በእርጅና፣ በተፈጥሮ እና በሰው ሠራሽ ምክንያቶች የሚያጋጥሟቸው በርካታ ችግሮች አሉ ነው ያሉት፡፡ ከችግሮች ጋር ተያይዞ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተደነገጉ ሕጎች መኖራቸውንም ተናግረዋል፡፡ ሕጎቹን መሠረት አድርጎ ለእነሱ የሚገባቸውን እንክብካቤ እና ፍቅር በመስጠት በኩል ጉድለቶች ስላሉ በዓሉ ሲከበር በማኅበረሰቡ ላይ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራዎች እንደሚሠሩ ገልጸዋል፡፡
‎አረጋውያን መሥራት አይችሉም የሚለውን አስተሳሰብ በመስበር ያላቸውን እምቅ አቅም ተጠቅመው በሚችሉት ሥራ እንዲሠማሩ ማድረግ አስፈላጊ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
‎‎በዓሉ በክልሉ በሚገኙ በሁሉም ዞኖች እና ወረዳዎች በንቅናቄ ይከበራል፤ በመጨረሻም የማጠቃለያ ፕሮግራም በክልል ደረጃ ይከናወናል ነው ያሉት።
‎‎በዓሉ ሲከበር የተለያዩ መድረኮችን በመፍጠር የአረጋውያን ደኅንነት እና ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ይሠራል ብለዋል፡፡ በአረጋውያን ላይ መልካም ሥራ የሚከውኑ ግለሰቦችን፣ ተቋማትን እና ሲቪክ ማኅበራትን እውቅና ይሰጣል ነው ያሉት፡፡
የማዕድ ማጋራት እና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ አረጋውያንን የመጠየቅ ተግባር የበዓሉ አንዱ አካል መኾኑን ገልጸዋል።
‎‎አረጋውያን ተደራጅተው መብታቸውን የሚያስከብሩበትን መንገድ ማመቻቸት እና ተጠቃሚነታቸውን እንዲያረጋግጡ ማድረግ ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚያስፈልግም አንስተዋል፡፡ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልኾኑ ተቋማት የአረጋውያንን ጉዳይ በዕቅዶቻቸው አካተው እንዲሠሩ እና ማኅበራዊ ኀላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
‎‎አረጋውያን ለሰላም ግንባታ የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱም ጠይቀዋል።
‎‎ዘጋቢ፡- ፍሬሕይወት አዘዘው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleኢትዮጵያ በቤተሰብ ዕቅድ ምጣኔ ውጤታማ ሥራዎችን ማከናወን ችላለች።
Next articleግብረ ገብነትን ተላብሶ ሕዝብን ማገልገል ይገባል።