
አዲስ አበባ፡ መስከረም 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ዕቅድ ቀን በወልቂጤ ከተማ እየተከበረ ነው።
ቀኑ “መሰናክሎችን ማስወገድ፣ አቅምን መገንባት የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ተደራሽነት ለሚገባቸው ሁሉ” በሚል መሪ መልዕክት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጉራጌ ዞን በወልቂጤ ከተማ በወልቂጤ ጤና ጣቢያ የተለያዩ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ነው።
በጤና ሚኒስቴር የቤተሰብ ዕቅድ የእናቶች እና ሕጻናት አፍላ ወጣቶች ጤና ዋና ሥራ አሥፈፃሚ ዶክተር ማርያማዊት አስፋው በቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት የተቀናጀ ሥራ በመሠራቱ ውጤቶች ተመዝግበዋል ብለዋል።
ይሁን እንጂ አሁንም የእናቶች እና የጨቅላ ሕጻናት ሞትን ለመቀነስ በርብርብ መሥራት ይስፈልጋል ነው ያሉት።
የአገልግሎት ተደራሽነቱን ለማሳደግ አገልግሎቱ በሁሉም ጤና ተቋማት ተደራሽ እንዲኾን እየተሠራ መኾኑንም አክለዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊ ተወካይ ማሙሽ ሁሴን በክልሉ ከ1ሺህ በላይ ጤና ኬላዎች የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎትን አካተው እንዲሠሩ መደረጉንም ገልጸዋል።
በ2017 በጀት ዓመት ብቻ ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ ሴቶችን የቤተሰብ ዕቅድ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም ተናግረዋል።
ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ ከ35 በመቶ በላይ የሚኾኑት የረጅም ጊዜ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ተጠቃሚ ናቸው ብለዋል።
የወልቂጤ ከተማ ከንቲባ ሙራድ ከድር ከተማዋ በጤና ተቋማት እናቶችን በማጎልበት በየደረጃው ያሉ የጤና ተቋማትን በግብዓት በማሟላት የእናቶች እና ሕጻናት ጤናን በመጠበቅ አርዓያ የሚኾነው የወልቂጤ ጤና ጣቢያ እንደኾነም አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ በቤተሰብ ዕቅድ ምጣኔ ባለፉት አራት ዓመታት ውጤታማ ሥራዎችን ማከናወን የቻለች ሲኾን በዚህም እ.ኤ.አ በ2000 ስድስት በመቶ የነበረው የእርግዝና መከላከያ ስርጭት በ2024 ወደ 42 ነጥብ 7 በመቶ ከፍ ብሏል ነው ያሉት።
በዘመናዊ መንገድ የእርግዝና መከላከያን የሚጠቀሙ ሴቶች ቁጥርም ከአራት ዓመት በፊት ከነበረው 600ሺህ ወደ 8ሚሊዮን ማሳደግ ተችሏል።
በዚህም በወሊድ ወቅት ያጋጥም የነበረውን የእናቶች ሞት፣ ያልተፈለገ እርግዝና እና ደኅንነቱ ያልተጠበቀ ውርጃ ምጣኔን በእጅጉ በመቀነስ ስኬታማ ሥራዎች መሠራታቸውንም መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ከተለያዩ ክልሎች የተውጣጡት የሥራ ኀላፊዎች እና እንግዶች የወልቂጤ ጤና ጣቢያን የጎበኙ ሲኾን በዓሉ በዓለም ለ18ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ10ኛ ጊዜ ነው የተከበረው።
ዘጋቢ፦ ቤተልሄም ሰለሞን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን