“ከትምህርት ወደ ኋላ ሊያስቀሩ የሚችሉ ችግሮችን በመቋቋም ነው ለውጤት የበቃሁት” ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበ ተማሪ

16
ባሕር ዳር: መስከረም 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ተማሪ ደሳለው ሞላ በእንጅባራ ከተማ የዛግዌ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ነው፡፡
ትምህርት ቤቱ በ2017 ዓ.ም ካስፈተናቸው የ12ኛ ክፍል ማጠቃለያ ፈተና ተፈታኝ ተማሪዎች ውስጥ 565 በማምጣት ከፍተኛ ውጤት አስመዝግቧል፡፡
ለዚህ ውጤት መሳካት የመጀመሪያው የእግዚብሔር ርዳታ ነው፤ በመቀጠል እኔ የማደርጋቸው ጥረቶች ነው ብሏል።
ቤተሰቦቼ በተለይም እነሱ ሳይማሩ የትምህርትን ጥቅም በመገንዘብ የ4:00 የእግር መንገድ እንጨት እና ቀለብ ወደ ምማርበት ተሸክመው በማመላለስ እና አይዞህ በማለት የሚያደርጉልኝ እገዛ ብርታት ኾኖኛል ነው ያለው፡፡
መምህራንም ጥያቄዎችን ቀድሜ በመሥራት እንድለማመድ በማድረግ፣ በግል ጭምር የሚያስፈልጉ ግብአቶችን በማሟላት እና በማመረታታት ከፍተኛ የኾነ እገዛ አድርገውልኛል ብሏል፡፡
አሁን ላይ በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ግጭቶች በመማር ማስተማሩ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ፤ እኔ ግን በችግር ውስጥም ኾኜ እንዴት የተሻለ ውጤት በማምጣት ከዚህ ችግር እራሴን ማውጣት እችላለሁ ብዬ በማሰብ ነበር በርትቼ የማጠናው ነው ያለው።
አሁን ላይ ያለውን ችግር እንደምክንያት በመቁጠር ከትምህርቴ ወደ ኋላ ማለት አላሰብኩም ነበር፡፡ ይህ ጥንካሬዬ ጭምር ነው ለውጤት እንድበቃ ያደረገኝ ብሏል፡፡
በዚህም ትምህርት ቤቱ፣ የእንጅባራ ከተማ አሥተዳደር እና የክልሉ ትምህርት ቢሮ የማበረታቻ ሽልማት ሸልሞኛል ነው ያለው፡፡
በዚህም በጣም ደስተኛ ነኝ ያለው ተማሪው ዩንቨርሲቲ ላይም የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ጥረት እንደሚያደርግ ተናግሯል፡፡
ማንኛውም ተማሪ በትምህርት ዘመኑ የተለያዩ ችግሮችን ሊያሳልፍ ይችላል፤ ሆኖም ችግሩን እንደምክንያት ቆጥሮ ወደ ኋላ ከመቅረት ይልቅ እንደመልካም አጋጣሚ በመቁጠር ዕቅድን ማሳካት ይገባል ብሏል።
በተጨማሪም ቤተሰቦቻችን ከልጅነት ጀምሮ እኛን አስተምረው ጥሩ ደረጃ ላይ ለማድረስ ያደረጉልንን ውለታ በማሰብ፤ በምን አይነት ውጤት ነው የወላጆቻችን ውለታ የምንመልስ የሚለውንም በማሰብ ከትምህርት ወደ ኋላ ሊያስቀሩ የሚችሉ ችግሮችን በመቋቋም ለውጤት መብቃት ይኖርብናል ነው ያለው።
የተማሪ ደሳለው ሞላ ታላቅ ወንድም ዲያቆን የኔው ሞላ
ከልጅነቱ ጀምሮ ለትምህርቱ ትኩረት የሚሰጥ፣ በባሕሪው የተመሰገነ፣ ለቤተሰቦቹ ታዛዥ ልጅ መኾኑን ገልጸዋል።
ከልጅነቱ ጀምሮ የሕክምና ትምህርት የማጥናት ሕልም እንዳለውም ተናግረዋል።
ሕልሙን ለማሳካት የሚያስፈልገውን የመማር ማስተማር ግብዓቶችን በማሟላት እና በምክር የማበረታቻ ሀሳቦችን በመስጠት እገዛ ያደርጉለት እንደነበር ተናግረዋል፡፡
በ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ከፍተኛ ውጤት በማምጣቱ መደሰታቸውን ገልጸዋል። ሕልሙን አውን እንዲያደርግ ድጋፍ እንደሚያደርጉለትም አመላክተዋል።
በእንጅባራ ከተማ የዛጉዌ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት
ቤት ምክትል ርእሰ መምህር ሀብታሙ ካሳሁን የዛጉዌ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚያስፈተናቸውን ተማሪዎች ውጤታማ ለማድረግ እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ከመደበኛው ክፍለ ጊዜ ውጭ ቅዳሜና እሁድን በመጠቀም ተማሪዎች እንዲበቁ ሥራ ተሠርቷል ነው ያሉት፡፡ይህ ድጋፍ ከተደረገላቸው ተማሪዎች ውስጥ ደግሞ ተማሪ ደሳለው አንዱ ነው ብለዋል።
ተማሪ ደሳለው በጣም ጎበዝ ተማሪ ነው፤ ጊዜውን በትክክል ይጠቀማል፣ ያነባል፣ ያልገባው ካለ ሰዓት ስለደረሰ ብቻ ወደ ቤቱ አይሄድም ነበር፤ መምህራንን ጠይቆ ተረድቶ ሲገባው ነው ወደ ቤት የሚሄደው ነው ያሉት።
በዚህም ከዘጠነኛ እስከ 12ተኛ ክፍል ያለው ውጤት 99 ነጥብ 9 ከመቶ እንደነበር አስታውሰዋል።
ለቀጣይም እንደ ተማሪ ደሳለው ያሉ ጥሩ ውጤት የሚያስመዘግቡ ተማሪዎችን ለማበረታታት ትምህርት ቤቱ ሽልማት በመስጠት የችቦ ርክክብ ሥነ ሥርዓት አካሂዷል ነው ያሉት።
ይህ የችቦ ርክክብ ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡ ተማሪዎች ለቀጣይ የማትሪክ ተፈታኞች የእነሱን አርዓያነት ይዘው እንዲወጡ ትልቅ ስንቅ እንዲኾናቸው ያደረግንበት ነው ብለዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየብሬል እጥረት ዐይነ ስውራን ተማሪዎችን እየፈተነ ነው።
Next articleኢትዮጵያ በቤተሰብ ዕቅድ ምጣኔ ውጤታማ ሥራዎችን ማከናወን ችላለች።