የብሬል እጥረት ዐይነ ስውራን ተማሪዎችን እየፈተነ ነው።

9
ባሕር ዳር፡ መስከረም 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ብሬል ለዓይነ ሥውራን ወሳኝ ጉዳይ ነው።
የዐይነ ስውራን የሃሳባቸው መከተቢያ የኾነው ብሬል አስፈላጊ መሳሪያ ነው። የዓለማቀፉ የዐይነስውራን ማኅበር መረጃ እንደሚያሳየው በዓለም ላይ 43 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች ዐይነ ስውራን ናቸው።
ከእነዚህ ዐይነ ስውራን መካከል ከ10 በመቶ እስከ 25 በመቶ ብቻ ናቸው የብሬል አቅርቦት የሚያገኙት።
በኢትዮጵያም ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ዐይነ ስውራን ቢኖሩም በብሬል እጥረት ምክንያት መፃፍ የማይችሉ ዐይነስውራን እየተፈጠሩ እንደሚገኙ ከአማራ ክልል አካል ጉዳተኞች ፌዴሬሽን ያገኘነው መረጃ ያስረዳል።
ዐይነ ስውራን የጽሑፍ ቋንቋቸው ብሬል እንደኾነ የሚናገረው የባሕርዳር ከተማ ነዋሪው ተማሪ ሀብተ ማሪያም አለልኝ በአማራ ክልል በብሬል እጥረት ምክንያት ጽሑፍ ለመፃፍ የሚቸገሩ ዐይነስውራን እየተፈጠሩ መኾኑን ተናግሯል።
በባሕር ዳር ፋሲሎ ትምህርት ቤት የ12 ክፍል ተማሪው ሃብተማሪያም አለልኝ ዐይነ ስውር ቢኾንም ከማንኛውም ሙሉ አካል ካለው ሰው ጋር መወዳደር እንደሚችል ተናግሯል።
እንደ ሀገር በተለያዩ መድረኮች አካቶ ትግበራ ይባላል፤ ነገር ግን አካቶ ማለት ጽንሰ ሃሳቡም ገና ግልጽ ያልኾነላቸው ብዙ ናቸው ነው ያለው።
አንድ ሥርዓተ ትምህርት ሲቀረጽ ሁሉንም የኅብረተስብ ክፍል ያማከለ መኾኑን የተናገረው ተማሪ ሀብተማሪያም “እኛ ግን እየተመዘን ያለነው ባልተሟላ ግብዓት ነው” ብሏል።
በተለይ ጉዳቱ ከአራተኛ ክፍል በላይ ባሉ ተማሪዎች ላይ ጎልቶ እንደሚታይ የገለጸው ተማሪ ሀብተማሪያም ከዛ በታች ባሉት ክፍል ላይ ዐይነስውራን ብቻቸውን ስለሚማሩ ችግሩ ያን ያክል የከፋ አይደለም ነው ያለው።
በጣና ሐይቅ የ9ኛ ክፍል ተማሪ አበባ ዘላለም “ዐይነስውር በመኾኔ ሳይኾን የሚያስፈልገኝን ማድረግ ባለመቻሌ አዝናለሁ፤ እንደ ማንኛውም ተማሪ ሁሉም ነገር ቢሞላልኝ እኔም ውጤታማ ነኝ” ብላለች።
በዲግሪ ተመርቀው ያሉ ዐይነስውራን ግን ደግሞ በብሬል መፃፍ የማይችሉ እህት ወንድሞቸን ማየት የተለመደ እንደኾነ ገልጻለች። ይህ ችግር መፈታት እንዳለበት ተናግራለች።
“ለዐይነስውራኑ ምንም አይነት ቁሳቁስ እየተሟላ አይደለም፤ በመቅረጸ ድምጽ እንሰማለን፤ ብዙ ጊዜ ደጋግመን ሰለምንሰማው እንደ ዐይናችን ጆሮችንን እንዳናጣ እፈራለሁ” ነው ያለችው።
የተለያዩ መድረኮች ላይ ችግሮቻች እንደሚነሱ የተናገረችው ተማሪዋ መፍተሔው ግን ቅርብ አልኾነም ብላለች። ለችግሩ ምላሽ እንዲሰጥም ጠይቃለች።
የአማራ ክልል አካል ጉዳተኞች ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ፍሬ ሰላም ዘገየ በአብዛኛው በክልሉ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ለዐይነስውራን ምቹ ካለመኾናቸው የተነሳ ለአካቶ ትግበራ መማር ማስተማር ሂደት ላይ ችግር እየፈጠረ መኾኑን ተናግረዋል።
ዐይነ ስውራኑ በአማራጭ በብሬል እጥረት ምትክ የድምጽ መሳሪያዎችን እየተጠቀሙ ትምህርታቸውን እንደሚከታተሉ ገልጸዋል። በዚህ ምክንያት ዐይነስውራኑ ከፍተኛ ለኾነ የጆሮ ሕመም መዳረጋቸውንም አንስተዋል።
በክልሉ የሕዝብ ቁጥር ሲጨምር የዐይነስውራን ቁጥርም በዚሁ ልክ እየጨመረ እንደሚሄድ የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ እንደየ ጉዳታቸው ለአካል ጉዳተኞች ቁሳቁስ ማሟላት ለመንግሥት ብቻ የሚተው ጉዳይ ሳይኾን የተለያዩ ድጋፍ ሰጭ በጎ አድራጊዎችንም የሚመለከት ነው ብለዋል።
ለአካል ጉዳተኞች እና ለዐይነስውራን የሚሰጠው ትኩረት እንደ ክልል እየላላ በመኾኑ ከዚህ በበለጠ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ገልጸዋል።
አካል ጉዳተኞችን እኩል ተወዳዳሪ ለማድረግ እና ልማትን ለማፋጠን ለአካልጉዳተኞች ቁሳቁስ ማሟላት እና ብቁ መምህራንን ማፍራት ተገቢ ነው ብለዋል።
አካል ጉዳተኞችን በአካታችነት ማስገባት የሁሉም ኅብረተሰብ እና ባለድርሻ አካላት ጉዳይ መኾኑንም አንስተዋል።
በአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የልዩ ፍላጎት እና አካቶ ትምህርት ባለሙያ ስንታየሁ እምሩ አካል ጉዳተኞችን ወደ ትምህርት ገበታ ለማምጣት ብዙ ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል።
በመጀመሪያ ደረጃ አካል ጉዳቱኞችን እንደ ጉዳታቸው አይነት እና መጠን መረጃ በማሠባሠብ ጉዳተኞቹ የሚያስፈልጋቸውን እንለያለን ያሉት ወይዘሮ ስንታየሁ በጉዳታቸው አይነት ድጋፍ ይደረጋል ነው ያሉት።
በየዓመቱ የድጋፍ መስጫ ማዕከል ለማቋቋም እየሠሩ እንደኾነም አስረድተዋል። ማዕከሉ አስፈላጊ ቁሳቁስ እንዲይዝ ተደርጎ እንደሚገነባም ገልጸዋል።
እንደ ክልል ከ1ኛ ክፍል እስከ 8ኛ ክፍል ላሉ ተማሪዎች መጻሕፍትን እና ብሬል እያሳተሙ እንደሚገኙም ተናግረዋል።
ከ9ኛ ክፍል እስከ 12ኛ ክፍል ላሉ 0ይነ ስውራን ተማሪዎች ግን መጻሕፍት የሚታተሙት በፌዴራል በመኾኑ ከነሱ ጋር በመነጋገር ችግሮች እንዲፈቱ እየተደረገ እንደኾነም ገልጸዋል።
የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ለአንድ ተቋም ብቻ የሚተው ባለመኾኑ ወላጆች፣ መምህራን፣ ባላሃብቶች፣ በጎ አድራጊዎች እና ባለድርሻ አካላት ተባብረው እንዲያግዟቸውም ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፦ ሰመሀል ፍስሀ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous article“ኢትዮጵያ ማኅበራዊ ጥበቃን የምትመለከተው እንደ በጎ አድራጎት ብቻ ሳይኾን እንደ መሠረታዊ መብት ጭምርም ነው” ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ.ር)
Next article“ከትምህርት ወደ ኋላ ሊያስቀሩ የሚችሉ ችግሮችን በመቋቋም ነው ለውጤት የበቃሁት” ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበ ተማሪ