
ደብረ ማርቆስ: መስከረም 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የእናት ደብረ ማርቆስ ሕጻናት መንደር የበጎ አድራጎት ድርጅት በወጣቱ የሕክምና ባለሙያ በትረማርያም ዘለቀ እና የሥራ ባለደረቦቹ ድጋፍ በደብረ ማርቆስ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አንድን ታዳጊ በማሳደግ ከዛሬ ስምንት ዓመት በፊት የተጀመረ በጎ ተግባር ነው።
የዚህ በጎ አድራጎት ድርጅት መሥራች እና ሥራ አስኪያጅ በተረማርያም ዘለቀ አንድን ሕጻን በማሳደግ የተጀመረው በጎ ተግባር ዛሬ ላይ በተለያየ መንገድ አሳዳጊ ለሌላቸው ሕጻናት መጠጊያ እና ተስፋ ወደ መኾን የተሸጋገረ መንደር ተመሥርቷል ብለዋል።
እናት ደብረ ማርቆስ የሕጻናት መንደር በጎ አድራጎት ድርጅት ከተመሠረተ ወዲህ አሳዳጊ የሌላቸውን ሕጻናት ተቀብሎ ከማሳደግ በተጨማሪ ወላጆችን በማፈላለግ ጭምር የማገናኘት ተግባራትን እንደሚያከናውንም በትረማርያም ገልጸዋል።
በበጎ አድራጎት ድርጅቱ የሚገኙ ሕጻናት ተገቢ እንክብካቤ እያገኙ መኾናቸውን የሚናገሩት በትረማርያም በሕጻናት መንደሩ አስተማሪዎች ተቀጥረውላቸው ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ታዳጊዎች መኖራቸውንም ተናግረዋል።
ለሕጻናት መንደሩ የአካባቢው ማኅበረሰብ፣ በሀገር ውስጥ እና በውጭ የሚኖሩ በጎ አድራጊዎች የሚያደርጉለት ድጋፍ አበረታች መኾኑን ነው የገለጹት።
በቀጣይም በመንደሩ የሚገኙ ሕጻናት እና ታዳጊዎችን ነገ ያማረ ለማድረግ ሕጻናቱ በጎ ልቦችን እና በጎ ተግባራት እንደሚሹም አብራርተዋል።
የኔሰው ብናልፍ እና አይናለም ወጋየሁ በእናት ደብረ ማርቆስ የሕጻናት መንደር የበጎ አድራጎት ድርጅት ሕጻናትን በመንከባከብ ተቀጥረው እያገለገሉ ነው፡፡ እነዚህ አሳዳጊዎች ሕጻናቱን ማሳደግ እና ከእነዚህ ሕጻናት ጋር ጊዜ ማሳለፍ የሚሰጠው ስሜት ከክፍያም በላይ ነው ብለዋል፡፡
በዚሁ የሕጻናት መንደር በፕሮጀክት ባለሙያነት እያገለገለ የሚገኘው ወጣት የኋላሸት ቻላቸው የሕጻናትን ነገ ለማሳመር በሚሠራ የበጎ አድራጎት ድርጅት ውስጥ ማገልገሉ የሚፈጥርለት የዓዕምሮ እርካታ ከፍተኛ መኾኑን ነግሮናል፡፡
የእናት ደብረ ማርቆስ የሕጻናት መንደር አገልጋዮች የእነዚህን ታዳጊዎች ነገ ያማረ ለማድረግ መልካም ልብና ትጋትን ይጠይቃልም ነው ያሉት፡፡
ይህን የሕጻናቱ የነገ ተስፋ ያማረ ለማድረግ በትጋት እየሠሩ መኾናቸውን እና ብሩህ የሕጻናቱን ዘመን በተስፋ እንደሚጠብቁም ገልጸዋል፡፡
በአንድ ወጣት የህክምና ባለሙያ በጎ ሃሳብ እና ተግባር እና በሥራ ባልደረቦቹ ድጋፍ አንድን ሕጻን በማሳደግ የተጀመረው በጎ ተግባር አሁን ላይ ብዙዎችን ታድጓል።
“ልጅ ከማሕጸን ብቻ ሳይኾን ከልብም ይወለዳል” የሚል መርሕን በመያዝ ዛሬ ላይ የእናት ደብረ ማርቆስ የሕጻናት መንደር በጎ አድራጎት ድርጅት ለበርካታ ሕጻናት ተስፋ እና መጠጊያ መኾን የቻለ መንደር እስከመኾንም ደርሷል።
ዘጋቢ:- ዘላለም አስፋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!