ከ600 ሺህ በላይ ሠራተኞችን ለመቀበል ዝግጅት እያደረገ መኾኑን የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አስታወቀ።

17
ሁመራ፡ መስከረም 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የምርት ብክነት እንዳይከሰት አስቀድሞ እየሠራ መኾኑን በአማራ ክልል የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ግብርና መምሪያ አስታውቋል።
በ2017/18 የምርት ዘመን በዞኑ ከ560 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች መሸፈኑን የመምሪያው ኀላፊ አወቀ መብራቱ ለአሚኮ ተናግረዋል። ከዚህ ውስጥ የሰሊጥ ድርሻ ከፍተኛ መኾኑንም አንስተዋል። በአሁኑ ወቅት ሰብሎቹን ለመሠብሠብ እየደረሱ በመኾኑ የዞኑ ግብርና መምሪያ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የምርት ብክነትን ለማስቀረት አስቀድሞ እየሠራ መኾኑን ነው አቶ አወቀ የገለጹት።
ከመስከረም 25 ጀምሮ ሰብል ሥብሠባው እንደሚጀምር ያስታወቁት መምሪያ ኀላፊው ለዚህም ከ600 ሺህ በላይ ሠራተኞች እንደሚያስፈልጉ አስታውቀዋል።
አካባቢው ፍጹም ሰላም መኾኑን ያነሱት አቶ አወቀ በአማራ ክልል እና በመላው ኢትዮጵያ ለሚገኙ ሥራ ፈላጊዎች ወደ አካባቢው መጥተው የእድሉ ተጠቃሚ እንዲኾኑም ጥሪ አቅርበዋል። ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሰው ኀይል ወደ አካባቢው ሲመጣ ሊያጋጥሙ የሚችሉ እንቅፋቶችን ለማስቀረት ከወዲሁ በመለየት እየተሠራባቸው እንደኾነም አስረድተዋል። የጤና፣ የምግብ እና ንጹህ የመጠጥ ውኃ አቅርቦትን ጨምሮ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ እየተሠራ ነው ብለዋል። የትራንስፖርት አገልግሎቱን የተሳለጠ ለማድረግም እየተሠራበት በመኾኑ ሠራተኞች ከየትኛውም አካባቢ እንዲመጡ ምቹ ኹኔታ እንደሚፈጠር ተመላክቷል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየብሔረሰብ አሥተዳደሩ የሰላም እና የልማት ሥራዎች እንዲሳለጡ የምክር ቤት አባላት ጉልህ ሚና እየተወጡ ነው።
Next articleልጅ ከማሕጸን ብቻ ሳይኾን ከልብም ይወለዳል።