የቅመማ ቅመም ምርት አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እያደረገ ነው።

7
ባሕር ዳር: መስከረም 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ‎ቅመማ ቅመም በኢትዮጵያ ባሕላዊ ምግቦች የሚዘወተሩ ግብዓቶች ናቸው። በኢትዮጵያ በርካታ የቅመማ ቅመም አይነቶች ይመረታሉ። ቅመማ ቅመም በስፋት ከሚመረትባቸው አካባቢዎች የአማራ ክልል አንደኛው ነው።
በአማራ ክልል ነጭ አዝሙድ፣ ጥቁር አዝሙድ፣ አብሽ፣ በርበሬ፣ ነጭ ሽንኩርት እና ሌሎችም 12 አይነት ቅመማ ቅመሞች የሚመረቱ መኾኑን ከክልሉ ግብርና ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
‎በአማራ ክልል የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ቅመማ ቅመም በስፋት በማምረት ይታወቃል። በዞኑ ነጭ አዝሙድ፣ ጥቁር አዝሙድ፣ አብሽ፣ በርበሬ፣ ነጭ ሽንኩርት በስፋት ይመረታሉ።
‎ወጣት አላቸው አድኖ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጣቁሳ ወረዳ ቅመማ ቅመም ያመርታል። አካባቢያቸው ለቅመማ ቅመም የተፈጥሮ ጸጋ ያለው መኾኑን ነግሮናል። በግማሽ ሄክታር ማሳ ላይ ቅመማ ቅመም እያለማ መኾኑን ገልጿል። እንደየ ቅመም አይነቱ ቢለያይም የሚሰጠው ምርት አዋጭ እና ገበያ ላይ ተፈላጊ መኾኑን ተናግሯል።
‎የቅመማ ቅመም ምርት አስፈላጊው ክትትል ከተደረገበት እና ማዳበሪያ በአግባቡ ከተጠቀሙ ምርታማነቱ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርግ መኾኑን ገልጿል። ነጭ አዝሙድ፣ ጥቁር አዝሙድ፣ አብሽ እና በርበሬ በአካባቢው በብዛት ይመረታል። ከሌሎች ሰብሎች ጋር ሲነጻጸር አዋጭ መኾኑን ነው የገለጸው፡፡ ወጣት አላቸው በሕይወቱ ለውጥ ማምጣቱንም ገልጿል። አሁን ላይ የአካባቢው አርሶ አደሮች በገበያ ላይ ተፈላጊ የኾኑ የቅመማ ቅመም አይነቶችን ለይተው እያመረቱ መኾኑን አንስቷል።
‎በግብርና ባለሙያዎች ምርታማነቱን ለማሳደግ ሙያዊ ድጋፍ ይደረጋል፤ ነገር ግን የማዳበሪያ አቅርቦት ችግር እንዳጋጠመ ጠቁሟል።
‎የጣቁሳ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት የአትክልት እና ፍራፍሬ መስኖ አጠቃቀም ቡድን መሪ አወቀ መከተ ወረዳው ቅመማ ቅመም ለማምረት እምቅ አቅም አለው ብለዋል። በተያዘው የመኸር ወቅት በወረዳው ከ13 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ቅመማ ቅመምን ጨምሮ በሆርቲካልቸር ዘር ተሸፍኗል ነው ያሉት።
‎አርሶ አደሮች ከዚህ በፊት ነጭ እና ጥቁር አዝሙድ በስፋት ያመርቱ ነበር ምክንያቱ ደግሞ የተሻለ ዋጋ እና ተፈላጊነት ስለነበረው ነው ብለዋል። አሁን ላይ ደግሞ በርበሬ ገበያ ላይ የተሻለ ተፈላጊነት ያለው በመኾኑ በሰፊው እየተመረተ እንደኾነ ገልጸዋል። ይህም አርሶ አደሮች ገበያ መር ኾነው እያመረቱ መኾኑን ያሳያል፡፡ ከተመረተ በኋላም የገበያ ትስስር ችግር እንደሌለ ተናግረዋል።
‎የቅመማ ቅመም ምርት ከሌሎች ሰብሎች ጋር ሲነጻጸር አዋጭ በመኾኑ የአርሶ አደሮች ሕይወት እየተቀየረ እና ቋሚ ሀብት እያፈሩ መኾኑን ገልጸዋል። ለዘርፉ ትኩረት ተሰጥቶ በኩታ ገጠም መልማት መጀመሩን አንስተዋል።
‎የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ የአትክልት እና ፍራፍሬ መስኖ አጠቃቀም ቡድን መሪ ሐውልቱ ታደሰ በዞኑ በሁሉም ወረዳዎች ቅመማ ቅመም ይመረታል ብለዋል። በመኸር ወቅት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራበት መኾኑንም ገልጸዋል።
‎ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ ለአርሶ አደሮች እና ለባለሙያዎች ሥልጠና ተሰጥቷል፤ ሁለት የቅመማ ቅመም ሰብሎች በርበሬ እና ነጭ ሽንኩርት ተለይተው ትኩረት ተሰጥቷቸው እየለሙ ነው ብለዋል፡፡
‎በርካታ ሄክታር መሬት በቅመማ ቅመም በዘር ተሸፍኗል። የአካባቢው አርሶ አደሮች ተጠቃሚ እንደሚኾኑ ይጠበቃል ብለዋል፡፡ ነጭ አዝሙድ እና ጥቁር አዝሙድ በማምረት እንደ ክልል እምቅ አቅም ያለው እና በፌደራል እስከ 20 በመቶ የሚኾነውን ድርሻ የሚይዝ መኾኑን ገልጸዋል፡፡
‎ለአርሶአደሮች እስከ ቀበሌ ድረስ የባለሙያ ድጋፍ እየተደረገ ነው ያሉት ቡድን መሪው የማዳበሪያ አቅርቦት ላይ እጥረት እንደነበር አንስተዋል፡፡ ኾኖም በሚፈለገው ደረጃ ባይኾንም የነበረውን ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች ለማዳረስ ጥረት መደረጉን ገልጸዋል፡፡
‎በአማራ ክልል የግብርና ቢሮ የመስኖ እና ሆርቲካልቸር ልማት ዳይሬክተር ይበልጣል ወንድምነው በክልሉ የቅመማ ቅመም ምርት ለማምረት እምቅ አቅም እንዳለ ተናግረዋል፡፡ የቅመማ ቅመም ምርት በመኸር ከሚለሙ ሰብሎች ውስጥ አንዱ ነው፤ መጠኑ እና አይነቱ ቢለያይም በሁሉም ዞኖች እንደሚመረት ተናግረዋል፡፡
‎እንደ ክልል በሀገር አቀፍ ደረጃ ትልቅ ድርሻ የሚይዙት በርበሬ፣ ነጭ ሽንኩርት፣ ጥቁር አዝሙድ፣ ነጭ አዝሙድ እና አብሽ ናቸው፡፡
‎የቅመማ ቅመም ምርታማነትን ለመጨመር እና አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ለማድረግ ከማሳ ዝግጀት እስከ ድህረ ምርት ድረስ ፓኬጅ ተዘጋጅቶ እየተተገበረ ነው ብለዋል፡፡ የአመራረት ሥራውን ለማዘመን ከጊዜ ወደ ጊዜ በምርምር የተደገፉ ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውን አንስተዋል፡፡
‎በየዓመቱ በቅመማ ቅመም አምራች አርሶ አደሮች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል ብለዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ የአርሶ አደሮች ግንዛቤ እያደገ መምጣቱ፣ የምርቱ ገበያ ላይ ተፈላጊነት እና አዋጭነት ምክንያቶቹ ናቸው ነው ያሉት፡፡
‎እንደ ጥቁር አዝሙድ ያሉ ቅመማ ቅመሞች በሄክታር ከ5 እስከ 6 ኩንታል የሚገኝ ቢኾንም ገበያ ላይ ግን የሚሸጥበት ዋጋ ከፍ ያለ በመኾኑ ከሌሎች ሰብሎች ጋር ሲነጻጸር አርሶ አደሮችን የሚጠቅም ነው ብለዋል፡፡
‎የቅመማ ቅመም ምርቶችን እሴት ጨምሮ መሸጥ ላይ የተጀመሩ ሥራዎች አሉ፡፡ ለአብነት በደንቢያ ወረዳ የጥቁር አዝሙድ ዘይት በመጭመቅ እየተሠራ ነው፤ ይህ ወደ ሌሎች እንዲሰፋ ይሠራል ነው ያሉት፡፡
‎ቅመማ ቅመም ማምረት ከፍተኛ ክትትል የሚጠይቅ እና በተለይም ደግሞ የተባይ አሰሳ ሥራን የሚፈልግ በመኾኑ የተሻለ ምርት ለማግኘት አርሶ አደሮች አስፈላጊውን ክትትል እንዲያደርጉ እና ባለሙያዎችም ትኩረት ሰጥተው እንዲደግፉ አሳስበዋል።
‎ዘጋቢ፡- ፍሬሕይወት አዘዘው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleቆሻሻ አወጋገድ ያስቀጣል!
Next articleአቢሲኒያ ባንክ ከታክስ በፊት 10 ቢሊዮን ብር በላይ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ።