
ባሕር ዳር: መስከረም 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ለሰው ልጅ መኖር አስፈላጊ ከኾኑ ነገሮች መካከል አንዱ ተስማሚ አካባቢ ነው። ሰዎች በከተሞች አካባቢ ተገቢ ባልኾነ የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት እየተፈተኑ እንደኾነ ይስተዋላል።
ካላቸው የሕዝብ ጥግግት አንጻርም በርካታ ተረፈ ምርቶች እና ቆሻሻዎች በደረቅ እና በፈሳሽ መልክ ወደ አካባቢው ይለቀቃሉ። ይህ ደግሞ የአካባቢ ብክለትን በማምጣት በአካባቢ ደህንነት እና በሰው ጤና ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እያስከተለ ይገኛል።
ይህንን ተገንዝቦ ኅብረተሰቡም ይሁን የሚመለከተው አሥፈጻሚ አካል ኀላፊነት ወስዶ ቆሻሻን በአግባቡ በማስወገድ በኩል ውስንነት መኖሩ ይነሳል። ሁሉም ሰው ንጹሕ እና ጤናማ በኾነ አካባቢ እንዲኖር በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 92 ላይ ተደንግጎ ይገኛል።
በአሚኮ የሕግ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት የሕግ ባለሙያ ፍቅር በለጠ ስለ ደረቅ ቆሻሻ አያያዝ እና አወጋገድ በወጣው አዋጅ 1383/2017 አንዱ መኾኑን ይገልጻሉ።
በዚህ አዋጅ መሠረት ደረቅ ቆሻሻ ማለት የማይፈለግ ተብሎ የተጣለ ማንኛውም ፈሳሽ ያልኾነ ቆሻሻ እንደኾነ ተቀምጧል ብለዋል የሕግ ባለሙያዋ።
በዚህ ትርጓሜ መሠረትም ደረቅ ቆሻሻ የሲጋራ ቁርጥራጭ፣ የሶፍት ወረቀት፣ ፌስታል፣ የጫት ገለባ፣ የፍራፍሬ ተረፈ ምርቶች፣ የትራንስፖርት ቲኬት፣ የሞባይል ካርዶችን፣ የማስቲካ እና ከረሜላ ሽፋኖች፣ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች፣ የውኃ ማሸጊያዎች፣ የእቃ መጠቅለያ የመሳሰሉትን ያጠቃልላል ነው ያሉት።
የሕግ ባለሙያዋ እንደሚሉት የአካባቢ ብክለትን ለመቀነስ የወጣው አዋጅ ቁጥር 300/1995 ሌላኛው የሕግ ማዕቀፍ መኾኑንም ያስረዳሉ።
በዚህ አዋጅ ላይ ደግሞ ፍሳሽ ማለት ተጣርቶም ይሁን ሳይጣራ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ ወደ አካባቢ የሚለቀቅ ቆሻሻ ውኃ ወይም ሌላ ፈሳሽ አሊያም ደግሞ ጋዝ ነው በማለት ይገልጸዋል።
የደረቅ ቆሻሻ አያያዝ እና አወጋገድ በአዋጁ ክፍል ሦስት አንቀጽ 10 በተቀመጠው መሠረት ማንኛውም ሰው ለዚህ ተብሎ ከተዘጋጀ ቦታ ውጭ ደረቅ ቆሻሻን ማስወገድ አይችልም በሚል አስቀምጦታል።
በአዋጁ እንደተገለጸው በከተሞች አካባቢ በሕዝብ ወይም በግል ይዞታ ላይ ደረቅ ቆሻሻን በማቃጠል ማስወገድ እንደማይቻልም ሕግ ባለሙያዋ ገልጸዋል፡፡ ለአንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውል ፕላስቲክ ማምረት፣ ለገበያ ማቅረብ፣ ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት፣ መሸጥ፣ ማከማቸት ወይም መጠቀም የተከለከለ ስለመኾኑም አስረድተዋል።
👉 አካባቢን የማጽዳት ግዴታ:-
ማንኛውም ሰው ከመኖሪያ ቤት ይዞታው ድንበር አንስቶ እስከ 20 ሜትር ባለው ርቀት ውስጥ ደረቅ ቆሻሻን የማጽዳት ኅላፊነት እንዳለበት በአዋጁ ተመላክቷል፡፡ የንግድ ተቋም ከይዞታው ድንበር አንስቶ ቢያንስ እስከ 50 ሜትር ባለው ርቀት ውስጥ ደረቅ ቆሻሻን የማጽዳት ኃላፊነት አለበት።
ደረቅ ቆሻሻ በከተማ አሥተዳደሮች በሚዘጋጁት የሕዝብ የጋራ መገልገያ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ገንዳዎች በጊዜያዊነት ማከማቸ አለበት። ማንኛውም ሰው የሞቱ እንስሳትን ለእነዚህ አይነት ቆሻሻዎች ተብሎ በተዘጋጁ ቦታ በጊዜያዊነት ማስቀመጥ እንደሚኖርበት አዋጁ ያስቀምጣል።
በየቆሻሻ ፈርጁ ተለይተው ምልክት የተደረገባቸው የቆሻሻ ማጠራቀሚያዎች አመቺ በኾነ ቦታ ማስቀመጥ እንደሚገባም በአዋጁ ተገልጿል፡፡ ማንኛውም ሰው ለደረቅ ቆሻሻ አያያዝ እና አወጋገድ አገልግሎት ክፍያ የመፈጸም ግዴታ አለበት፡፡
👉 አሥተዳደራዊ ቅጣት
በአዋጁ አንቀጽ 25 ስር ማንኛውም ሰው የፕላስቲክ ከረጢት ከተጠቀመ ወይም ይዞ ከተገኘ ወይም ማንኛውም ሰው አንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውል የፕላስቲክ ከረጢት ይዞ ከተገኝ ከ2,000 እስከ 5,000 ብር እንዲቀጣ ይደነግጋል፡፡
ቆሻሻ ያመረተ ወይም ወደ ሀገር ውስጥ ያስገባ፣ ለገበያ ያቀረበ ወይም የሸጠ፣ ለንግድ ዓላማ ያከማቸ ወይም ይዞ የተገኘ ከ50,000 ብር በማያንስ እና ከ200,000 ብር በማይበልጥ የገንዘብ መቀጮ እንዲኹም ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት እንዲቀጣ አዋጁ ያዝዛል፡፡
በአዋጁ አንቀጽ 5 ላይ ስለ ቆሻሻ አያያዝ በግልጽ ተቀምጧል። ብክለትን ወይም ሌላ አካባቢያዊ ጉዳትን ሊያስከትል በሚችል ተግባር ላይ የተሰማራ ሰው የቆሻሻ መመንጨትን ለማስወገድ ወይም ወደ ተፈላጊው መጠን ለመቀነስ በባለስልጣኑ ወይም በሚመለከተው የክልል የአካባቢ መሥሪያ ቤት ትዕዛዝ መሠረት ቆሻሻን መልሶ በጥቅም ላይ ለማዋል በሚያስችሉ ዘዴዎች መጠቀም አለበት።
የተቀናጀ የከተማ ቆሻሻ አያያዝ ሥርዓትን በማውጣት የከተማ ቆሻሻ መሠብሠቡ እና መጓጓዙ አስፈላጊ ኾኖ ሲገኝም በጥቅም ላይ መዋሉንም አልያም ደግሞ መምከኑን ወይም ጉዳት እንዳያመጣ ተደርጎ መወገዱን ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል።
ለሕዝብ ክፍት የኾነ ቦታን የሚያሥተዳድር ማንም ሰው ምን ጊዜም በቂ እና ተስማሚ የመጸዳጃ ቤት፣ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ እቃዎች እና አስፈላጊ የኾኑ ሌሎች መገልገያዎች በቦታው መዘጋጀታቸውን ማረጋገጥ እንዳለበትም ተገልጿል።
አዋጁን ተላልፎ ጥፋቱን የፈጸመ ሰው ከ5 ሺህ ብር በማያንስ እና ከ10 ሺህ ብር በማይበልጥ የገንዘብ መቀጮ ወይም ከአንድ ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት ወይም በሁለቱም እንደሚያስቀጣ ነው የገለጹት።
ዘጋቢ: አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!