“አቅም እያላቸው ፈተና ያልወሰዱ ተማሪዎች መኖራቸው የሰላምን አስፈላጊነት ይበልጥ ያሳያል”

13
ባሕር ዳር፡ መስከረም 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በ2017 የትምህርት ዘመን በ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች የዕውቅና እና የሽልማት ሥነ ሥርዓት አካሂዷል፡፡
በሥነ ሥርዓቱ የተሸለሙት 500 እና በላይ ነጥብ ያስመዘገቡ 452 ተማሪዎች ናቸው፡፡
ከተሸላሚዎቹ መካከል ተማሪ መልካሙ ውድነህ 543 ነጥብ በማግኘት ተሸልሟል፡፡ ባለፉት ዓመታት በአካባው በነበረው ግጭት ምክንያት አንድ ዓመት ትምህርቱን አቋርጦ ወደ ሌላ ቦታ በመሄድ ትምህርቱን ቀጥሎ ነው ለውጤት የበቃው፡፡ ከ500 በላይ ነጥብ ለማስመዝገብ አቅዶ መማሩን እና ጠንክሮ ማጥናቱንም ገልጿል፡፡
የክልሉ ትምህርት ቢሮም ድጋፍ ማድረጉን አስታውሶ የሥነ ልቦና ግንባታ እንደተደረገላቸውም ነው ተማሪ መልካሙ የገለጸው፡፡ በዚህም ጠናክሮ ትምህርቱን ማጥናቱን ነው ያስረዳው፡፡
የችግርን አስተማሪነት እና መፍትሄ አፈላላጊነት የጠቀሰው ተሸላሚው ተማሪ ቀጣይ ተፈታኝ ተማሪዎችም በጽናት መማር እንዳለባቸው መክሯል፡፡ ሀገር ለማጽናትም ትምህርትን የሚተካ እንደሌለም ገልጿል፡፡
ሌላኛዋ ተሸላሚ ተማሪ አርሴማዊት ተስፋዬ ከሰሜን ሸዋ 515 ነጥብ አስመዝግባለች፡፡ ወቅታዊው የጸጥታ ችግር በትምህርቷ ላይ ተጽዕኖ ቢኖረውም ጫናውን በመቋቋም ማጥናቷን ገልጻለች፡፡
ተማሪ አርሴማዊት “አቅም እያላቸው በጸጥታ ችግር ምክንያት ፈተና ያልወሰዱ ተማሪዎች መኖራቸውን ሳይ የሰላምን አስፈላጊነት ይበልጥ ተረድቻለው” ነው ያለችው።
የሀገር ሰላም መኾን ለሁሉም እንደሚጠቅምም መረዳቷን ተናግራለች፡፡
ሕክምና ማጥናት የምትፈልገው ተማሪ አርሴማዊት ተማሪዎች ተስፋ ሳይቆርጡ እና ዓላማ አስቀምጠው መማር እና ማጥናት እንደሚገባቸውም መክራለች፡፡
ወይዘሮ ሃያት ሰኢድ ከሰሜን ጎንደር የትንሽ ወንድሟን ሽልማት ለማጀብ እና ደስታውን ለማድመቅ በመድረኩ ተገኝተዋል፡፡
ወንድማቸው ተማሪ አህመድ ሰኢድ 517 ነጥብ በማስመዝገብ በዞኑ ከፍተኛ ውጤት ካመጡት ውስጥ መኾኑንም ነው የተናገሩት፡፡ በዚህም ደስተኛ እንደኾኑ ጠቁመዋል፡፡
ወይዘሮ ሃያት ወንድማቸው ተማሪ ሰኢድ ጥሩ ውጤት እንዲያገኝ አበርክቶ የነበራቸውን መምህራኖቹን፣ የትምህርት መሪዎችን እና የደባርቅ ዩኒቨርሲቲን አመሥግነዋል፡፡
ባሕር ዳር ከተማን አላውቃትም ነበር ያሉት ወይዘሮ ሃያት ለማየት የቻልኩትም ወንድሜ ጥሩ ውጤት ስላመጣ ነው ብለዋል፡፡
ወደፊትም ወንድማቸው የተሻለ ሰው ኾኖ ቤተሰቡን እና ሀገሩን እንዲጠቅም ለማድረግ ክትትል እና ድጋፍ ማድረጋቸውን እንደሚቀጥሉም ነው ያረጋገጡት።
ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየሴት መሪዎች ፎረም ዓመታዊ ጉባኤ እየተካሄደ ነው።
Next articleቆሻሻ አወጋገድ ያስቀጣል!