
ባሕር ዳር: መስከረም 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ማዕከላዊ ዞን ሴት መሪዎች ፎረም ዓመታዊ ጉባኤውን በባሕር ዳር ከተማ እያካሔደ ይገኛል።
በክልሉ ከሁሉም የፖለቲካ ፖርቲዎች የተውጣጡ ሴት መሪዎችም በጉባኤው ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ።
የአማራ ክልል ማዕከላዊ ዞን ሴት መሪዎች ፎረም ሰብሳቢ እና የአማራ ክልል ሴቶች፣ ህጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ ፎረሙ ሴት መሪዎች ልምዳቸውን የሚለዋወጡበት እና እርስ በርስ የሚደጋገፉበት ነው ብለዋል።
በተለይም በችግር ጊዜ በታችኛው መዋቅር ላይ ያሉ ሴት መሪዎች ብቃታቸውን ለማሳደግ፣ ለመደገፍ እና በቀጣይ ለሚካሄደው ምርጫ እንዴት ይዘጋጁ በሚለው ዙሪያ ለመመካከር የተዘጋጀ ጉባኤ መኾኑንም ነው የተናገሩት።
የዕለቱ የክብር እንግዳ እና በአማራ ክልል ምክር ቤት የሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አበራሽ ታደሰ አሁን ባለው ኹኔታ በአመራርነት በኩል የሴቶች ተሳትፎ ዝቅተኛ በመኾኑ ብዙ መሠራት አለበት ነው ያሉት።
ችግሮችን ተቋቁመው የሚዘልቁ ሴት አመራሮች እንዳሉ ሁሉ በተለያዩ ጫና ውስጥ ወደኋላ የሚቀሩትን መደገፍ እና ማብቃት ይገባል ብለዋል።
ሁሉም ሴት መሪዎች በየተቋማቸው ሴቶችን የማብቃት፣ የማጠናከር እና የማደራጀት ኀላፊነት እንዲወጡ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ፦ ፍሬሕይዎት አዘዘው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!