
ባሕር ዳር: መስከረም 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የልማት እና በጎ አድራጎት ተራድኦ ኮሚሽን አማራ ክልል ክላስተር ማሥተባበሪያ ጽሕፈት ቤት በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር በሚገኙ 10 ጤና ጣቢያዎች ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
አጠቃላይ አፈጻጸሙን በተመለከተም ዛሬ ላይ የውይይት መድረክ በባሕር ዳር ከተማ አካሂዷል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የልማት እና በጎ አድራጎት ተራድኦ ኮሚሽን የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የክትባት ቴክኒካል አሲስታንት አማረ ታከለ ኮሚሽኑ ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር ላለፉት ዓመታት በሰላም እና ደኅንነት፣ በምክር አገልግሎት፣ በሰብዓዊ እርዳታ እና በሥርዓተ ጾታ ዙሪያ ሢሠራ ቆይቷል ብለዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የክትባት እና የወረርሽኝ ቅኝት እና አሰሳ ላይ እየሠራ እንደሚገኝም ገልጸዋል። ከግንቦት 1/2017 ዓ.ም እስከ መስከረም 30/2018 ዓ.ም ድረስ በባሕር ዳር ከተማ በሚገኙ 10 ጤና ጣብያዎች ላይ ለክትባት ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ ነው ብለዋል።
በዚህም በከተማው ውስጥ 406 የሚኾኑ ክትባት አግኝተው የማያውቁ ሕጻናትን አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉን ተናግረዋል።
ተፈናቃዮችን፣ የጎዳና ተዳዳሪዎችን እና ሴተኛ አዳሪዎችን የክትባቱ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም ገልጸዋል።
የ”ሴቭ ዘችልድረን” የክትባት ዳይሬክተር ኀላፊ ምዕራፍ ሰለሞን ክትባት የሕጻናትን ሕመም እና ሞት ከሚቀንሱ የጤና አገልግሎቶች በግንባር ቀደም የሚጠቀስ መኾኑን ገልጸዋል።
ሴቭ ዘችልድረንም በኢትዮጵያ ለረጅም ዓመታት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የክትባት ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ነው የተናገሩት። ይህ በመኾኑም የክትባቱ ሽፋን እንዲጨምር ማድረጉን ገልጸዋል።
ይሁን እንጅ ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ ደግሞ በሰው ሠራሽ እና በተፈጥሮ ችግሮች ምክንያት ኢትዮጵያ ክትባት ያልጀመሩ እና ክትባት ጀምረው ያልጨረሱ ሕጻናት ከሚገኝባቸው ሀገራት ውስጥ አንዷ መኾኗን ገልጸዋል።
እነዚህን ሕጻናት ተደራሽ ለማድረግ ሴቭ ዘችልድረን ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት እየሠራ መኾኑንም ተናግረዋል። በክልሉም ክትባት ያላገኙ በርካታ ሕጻናት እንደመኖራቸው ትኩረት ተሰጥቶ ሊሠራ ይገባል ነው ያሉት።
የሲ.ሲ.አር.ዲ.ኤ ኮር ግሩፕ ፓርትነር ፕሮጀክት ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር ሙሉቀን አስረስ ፕሮጀክቱ ባለፉት ዓመታት ፖሊዮን ለማጥፋት ሢሠራ መቆየቱን ገልጸዋል። በተለይም ደግሞ የድንበር አካባቢዎች በሚገኙ ወረዳዎች የክትባት ሥራዎችን እየደገፈ መኾኑን ገልጸዋል።
በሰው፣ በእንስሳት እና በአካባቢ ጤና ላይ በክልሉ 56 ወረዳዎች ላይ ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በመተባበር እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። ባለፉት ወራትም ተራድኦ ኮሚሽኑን በመደገፍ ሕጻናት ክትባት እንዲያገኙ ሲያደርግ ቆይቷል ነው ያሉት።
በአማራ ክልል ጤና ቢሮ የእናቶች፣ ሕጻናት እና የአፍላ ወጣቶች ዳይሬክተር መልሰው ጫንያለው ኢትዮጵያ ያልተከተቡ ሕጻናትን በመያዝ በአፍሪካ ሁለተኛ ናት ብለዋል። የአማራ ክልል ደግሞ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደተቀመጠ ገልጸዋል።
ለዚህ ደግሞ የኮሮና ወረርሽኝ፣ የሰሜኑ ጦርነት፣ አሁን ላይ በክልሉ የተከሰተው ግጭት የክትባት ሂደቱን በተፈለገው መንገድ ለመሥጠት ፈታኝ አድርጎት ቆይቷል ነው ያሉት።
ባለፉት ወራት ክትባት ያልጀመሩ እና ጀምረው ያቋረጡ ሕጻናትን ተደራሽ ለማድረግ ከመደበኛው ክትባት ባለፈ በዘመቻ ቤት ለቤት ጭምር እንዲሰጥ ተደርጓል ብለዋል።
ይሁን እንጅ አሁንም በክልሉ 337 ሺህ የሚደርሱ ክትባት ያላገኙ ሕጻናት መኖራቸውን ነው ያነሱት። ያልተከተቡ ሕጻናትን ለመድረስ ከጥቅምት/2018 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት ሦስት ወራት በክልሉ በዘመቻ ጭምር ክትባቱ እንደሚሰጥም ገልጸዋል።
ሕጻናትን ማስከተብ የሁሉም ኀላፊነት ሊኾን እንደሚገባም አሳስበዋል።
ዘጋቢ:- ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!