
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 05/2012 ዓ.ም (አብመድ) በሰሜን ሸዋ ዞን አሳግርት ወረዳ የንጽሕና መጠበቂያ በማምረት የተሰማሩ ወጣቶች የገበያ ትስስር ችግር እንደገጠማቸው ለአብመድ ተናግረዋል፡፡
በአሳግርት ወረዳ አቶ ደምሰው አድምቀው እና ጓደኞቹ ሳሙና እና ሳኒታይዘር በማምረት ሥራ ላይ ተሰማርተው ለሌሎችም የሥራ ዕድል ፈጥረዋል፡፡ ወጣቶቹ ከዩኒቨርሲቲ እና ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት ያገኙትን ዕውቀት ወደ ተግባር በመቀየር የሥራ ዕድል ፈጥረዋል፡፡ አቶ ደምሰው ሽንቁጤ በ2011 ዓ.ም ነበር ከአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ በኬሚስትሪ የትምህርት መስክ የተመረቀው፤ ሥራ ከመፈለግ ሥራ ፈጣሪ በመሆን በዚያው ዓመት ሳሙና እና ሳኒታይዘር ወደ ማምረት መግባቱን ተናግሯል፡፡ ለሥራቸው የመነሻ ካፒታል 10 በመቶ ከግል እና 90 በመቶን ደግሞ በብድር እንዳገኙ ተናግሯል፡፡ ሥራውን ሲጀምሩ የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት ሥራ መጀመር የሚያስችል የምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል፤ ወጣቶቹ የልብስ፣ እጅ፣ የዕቃ፣ የመስታውት እና የሴራሚክ ማጽጃ ሳሙናዎችን እያመረቱ ነው፡፡
በቀን 2 ሺህ ሊትር ፈሳሽ ሳሙና ማምረት እንደሚችሉ ያስረዱት ወጣቶቹ የአንድ ቀን ምርታውን እንኳ በአራት ወራት ሸጠው እንደማይጨርሱ ተናግረዋል፡፡ “የገበያ ትስስር አለመኖሩ የተበደርነውን ብድር እንኳን ለመመለስ እንድንቸገር አድርጎናል” ብለዋል ወጣቶቹ፡፡
የማታወርቅ ሽንቁጤም ሥራውን በጀመሩበት ወቅት በቀን እስከ ስድስት ሺህ ብር ሽያጭ ያከናውኑ እንደነበርና አሁን በቀን እስከ 300 ብር ብቻ እንደሚሸጡ ተናግራለች፡፡ ለገበያው መቀነስ የምርታቸው ከፍተኛ መሆንና የወረዳው ሕዝብ ፍላጎት በጥቂት ምርት መሟላት እንደሆነ ተናግራለች፡፡ ከወረዳው ውጭ ወደ አጎራባች ከተሞች የገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸውም ጠይቃለች፡፡
የአሳግርት ወረዳ ቴክኒክ እና ሙያ ኢንተርፕራይዞች ልማት ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ ተስፋዬ ወርቁ ለወጣቶቹ መነሻ ካፒታል፣ የመሥሪያ እና መሸጫ ቦታ ጽሕፈት ቤቱ እንዳመቻቸላቸው ገልጸዋል፡፡ የገበያ ትስስር ለመፍጠር ሁሉም የመንግሥት ሴክተር መሥሪያ ቤቶች ግዥ ከማኅበራቱ እንዲፈጽሙ የድጋፍ ደብዳቤ እንደተጻፈም ተናግረዋል፡፡ “በቀጣይ ገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸው የተሻለ የመፍትሔ አቅጣጫ እናስቀምጣለን” ብለዋል ምክትል ኃላፊው፤ ወጣቶቹ የራሳቸውን የገበያ አማራጭ በመፈለግ ዘላቂ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ለመሆን መሥራት እንዳለባቸውም አስረድተዋል፡፡
የአሳግርት ወረዳ ቴክኒክ እና ሙያ ኢንተርፕራይዞች ልማት ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ ተስፋዬ ወርቁ እንደተናገሩት በወረዳው በበጀት ዓመቱ በከተማ አካባቢ ለሚገኙት 466 ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ዕቅድ ተይዟል፤ እስካሁን ለ435 ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል፡፡ በገጠር ደግሞ ለ2 ሺህ 855 ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር አቅደው እንደነበርና ሙሉ በሙሉ ማሳካት እንደቻሉ ምክትል ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡ ለወረዳው ከተመደበው ተዘዋዋሪ ፈንድ 12 ሚሊዮን 265 ሺህ 752 ብር 65 ኢንተርፕራይዞች ወደ ሥራ እንደተሰማሩም ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡