የባሕር ዳር ከተማን የጎብኝዎች ማዕከል ለማድረግ እየተሠራ ነው።

4
ባሕር ዳር: መስከረም 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ “ቱሪዝም ለዘላቂ ሽግግር” በሚል መሪ መልዕክት የዓለም የቱሪዝም ቀንን በምክክር መድረክ አክብሯል።
የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኀላፊ ዓባይ መንግሥቴ ማኅበረሰቡን ያሳተፈ የቱሪዝም ልማት ሥራ ዘላቂ ለውጥ ለማምጣት ያስችላል ብለዋል። በባሕር ዳር ከተማ ያሉትን ተፈጥሯዊ እና ባሕላዊ የቱሪዝም ምርቶችን ለይቶ መያዝ እና ማስፋት እንደሚገባ ገልጸዋል። የክልሉ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮም ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል። አስጎብኝዎች በዕውቀት የተካኑ ኾነው ገጽታን የሚገነቡ መኾን እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል። የክልሉን የቱሪዝም ሀብት ለማስተዋወቅ ጥረት እየተደረገ መኾኑንም ጠቁመዋል።ቱሪዝም ሰላምን ይፈልጋል ያሉት ምክትል ኀላፊው ጎብኝዎች በየትኛውም ቦታ ተንቀሳቅሰው በሰላም እንዲዝናኑ እና እንዲጎበኙ ሁሉም ርብርብ ሊያደርግ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ ጋሻው እንዳለው ከተማዋ ሰፊ የቱሪዝም ሀብት ያለበት ከተማ መኾኗን አንስተዋል። ከተማዋ ካሏት የተፈጥሮ ጸጋዎች በተጨማሪ በከተማ አሥተዳደሩ በርካታ የቱሪስት መዳረሻዎች እየተስፋፉ መኾናቸውንም ገልጸዋል። ያላትን ጸጋ መሠረት በማድረግ ባሕር ዳር ከተማን የጎብኝዎች ማዕከል ለማድረግ እየተሠራ መኾኑን አመላክተዋል። የኮንፈረንስ ቱሪዝምን ለማስፋፋት የሆቴል ኢንቨስትመንት ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ መኾኑን አንስተዋል። ለቱሪስቶች የተመቹ ሆቴሎች፣ ሎጂዎች እና የመሠብሠቢያ አዳራሾች እንዲስፋፉ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መኾኑን ጠቁመዋል።
የጣና ሐይቅ የታሪክና የሀገር በቀል ዕውቀት መድብል ነው ያሉት ኀላፊው ብዙ የሚነገርላቸው የጣና ሐይቅ እና አካባቢው ጸጋዎችን አልምቶ ለመጠቀም ከአጋር አካላት ጋር እየተሠራ መኾኑን አንስተዋል። በከተማዋ የሚገኙ የቱሪዝም ሀብቶችን በማልማት ከተማዋ ማግኘት የሚገባትን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንድታገኝ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል። በመድረኩ የተሳተፉት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ዋና ጸሐፊ መልአከ ብርሃን ፍስሀ ጥላሁን ቤተ ክርስቲያኗ በርካታ ቅርሶችን እና የመስህብ ሀብቶችን ጠብቃ ያቆየች መኾኗን ተናግረዋል። የብራና መጻሕፍትን፣ ሀገር በቀል እጽዋትን፣ የነገሥታትን ስጦታዎችን ለአብነት አንስተዋል።
የሚጎበኙት ቅርሶች በአንድ ማዕከል በማሰባሰብ ለጎብኝዎች ማቅረብ ቢቻል የተሻለ የቱሪዝም እድገትን ለማምጣት እንደሚያግዝ አንስተዋል። ጎብኝዎች ሲመጡ በዕውቀት ላይ በመመሥረት ማስተዋወቅ እንደሚገባም አንስተዋል። የናቡ ኢትዮጵያ የአቅም ግንባታ አማካሪ ባይህ ጥሩነህ በባሕር ዳር ከተማ እና አካባቢው የጣናን እና አካባቢው እንዲጠበቅ እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል። በጣና ሐይቅ ውስጥ ያሉት ቅርሶች እና የመስህብ ሀብቶች ተጠብቀው እንዲተዋወቁ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑን አመላክተዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“የእናንተ ውጤትም ችግርን የማሸነፍ እሳቤ ነው” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)
Next article“በችግር ውስጥም ኾነው ስኬታማ የኾኑ ተማሪዎች ምሥጋና ይገባቸዋል” ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር)