“ሀገሬን የሚጠቅም ሥራ ለመሥራት ተዘጋጅቻለው” ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበ ተማሪ

34
ጎንደር፡ መስከረም 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ላይ የተሻለ ውጤት መመዝገቡ ተገልጿል።
በማዕከላዊ ጎንደር ዞን አይከል ከተማ የዋርካ በር ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ እንደግ ባሻ በ2017 የትምህርት ዘመን በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በተፈጥሮ ሳይንስ 568 በማምጣት በዞኑ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ ችሏል። “ዓለም በቴክኖሎጂ መልኳ እየተቀየረ ነው” ያለው ተማሪ እንደግ “በቀጣይ ሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ በመማር ሀገሬን የሚጠቅም ሥራ ለመሥራት ተዘጋጅቻለው” ሲል ሃሳቡን ለአሚኮ ተናግሯል። ከፍተኛ ውጤት እንዲያስመዘግብ ከራሱ ጥረት በተጨማሪ የወላጆቹ እና የመምህራኑ ድጋፍ ወሳኝ እንደነበረ ተናግሯል።
በዞኑ ከፍተኛ ውጤት የተመዘገበበት በአይከል ከተማ የዋርካ በር ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አየልኝ አስፋው በ2017 የትምህርት ዘመን 235 ተማሪዎችን ትምህርት ቤቱ አስፈትኖ 34 ከመቶ ሚኾኑት ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚያስገባቸውን ውጤት ማስመዝገባቸውን ገልጸዋል። ከአዳር ጥናት ጀምሮ፣ ወርክ ሽቶችን በማዘጋጀት እና የተማሪዎችን የእርስ በእርስ ግንኙነት በማሳደግ እንዲተጋገዙ በመደረጉ ተማሪዎች ውጤታማ እንዲኾኑ እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ክንዱ ዘውዱ ዞኑ በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በተፈጥሮ ሳይንስ እና ማኅበራዊ ሳይንስ 8ሺህ 400 በላይ ተማሪዎችን ማስፈተኑን ገልጸዋል። እንደ ዞን የተሻለ ውጤት መመዝገቡንም ነው መምሪያ ኀላፊው ክንዱ ዘውዱ የተናገሩት።
በተያዘው ዓመት የመልቀቂያ ፈተናውን ከወሰዱት ውስጥ 16 ተማሪዎች ከ500 በላይ ውጤት ማምጣት መቻላቸውንም አብራርተዋል።
ዞኑ በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ኾኖ የተሻለ ውጤት ማስመዝገቡንም ነው ያስገነዘቡት። በዞኑ የነበረውን ችግር ተቋቁመው የተሻለ ውጤት እንዲመጣ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ተቋማት እና አጋር አካላት የዞኑ ትምህርት መምሪያ ምሥጋና አቅርቧል።
ዘጋቢ: ዳንኤል ወርቄ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleሰላምን የሚነሱ ተልዕኮ ተሸካሚ የውስጥ ተላላኪዎችን በኅብረት መታገል ያስፈጋል።
Next articleየሕዝብን የመልማት ፍላጎት የሚያሳካ ዕቅድ በማቀድ ወደ ሥራ መግባት ወሳኝ ነው።