
ደሴ፡ መስከረም 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የደሴ ከተማ አሥተዳደር በወቅታዊ የጸጥታ ጉዳይ ላይ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከታዋቂ ግለሰቦች እና ከልዩ ልዩ የኀብረተሰብ ክፍሎች ጋር ምክክር እያካሄደ ነው።
በመድረኩ ሃሳብ የሰጡ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች የሀገሪቱን መለወጥ እና ያላትን ተጽዕኖ ፈጣሪነት የማይወዱ ጠላቶች ከሀገር ውስጥ ተላላኪዎቻቸው ጋር ሌት ከቀን እየሠሩ ነው ብለዋል። ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በስኬት ከማጠናቀቅ በተጨማሪ የባሕር በር ይገባናል ጥያቄን ለዓለም ሕዝብ ሀገሪቱ በማቅረቧ ይህን የማይፈልጉ ጠላቶች ተልዕኮ ተሸካሚ የውስጥ ተላላኪ ጽንፈኞችን በመጠቀም ችግር እየፈጠሩ በመኾኑ በኅብረት መታገል ያስፈልጋል ነው ያሉት። የከተማዋ ሰላም የሚረጋገጠው በነዋሪዎቿ ኅብረት ነው ያሉት ነዋሪዎቹ ከወትሮው በተለየ በንቃት በመሳተፍ የተጀመሩ የልማት ሥራዎች ዳር እንዲደርሱ ከፊት ቆሞ መሥራት እንደሚገባም ነው አስተያየት የሰጡት።
በቀጣይ ከተማ አሥተዳደሩ ጠንካራ አደረጃጀት በመፍጠር እና በማሠልጠን አካባቢያችንን እንድንጠብቅ ሊያግዘን ይገባል ብለዋል የውይይቱ ተሳታፊዎች። በብልጽግና ፓርቲ የደሴ ከተማ አሥተዳደር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አሸናፊ ዓለማየሁ ሀገር አፍራሽ ጽንፈኞች የጋላቢዎቻቸውን ከንቱ አጀንዳ ተሸክመው ቢሯሯጡም ካስቀመጥነው ታላቅ ሀገራዊ ግብ ለአፍታ አያዘናጉንም ብለዋል። ጽንፈኞች የማንኛውም ሃይማኖት ወኪል አይደሉም ያሉት አቶ አሸናፊ ለዚህ ማሳያው ለታፈሩ እና ለተከበሩ የሃይማኖት አባቶች ጭምር የማስፈራሪያ መልዕክት ይልካሉ፤ ይገድላሉ፣ አማኙን ይዘርፋሉ ሲሉ ተናግረዋል።
በመኾኑም የሃይማኖት ተቋማት የጽንፈኞች መደበቂያ መኾን እንደሌለባቸው አመላክተዋል። አንድ ከተማ በጸጥታ ኀይል ብቻ አይጠበቅም ያሉት ኀላፊው የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ለከተማቸው ሰላም ከወትሮው በላቀ እንዲሠሩም ጠይቀዋል።
የደሴ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ የታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በስኬት በማጠናቀቅ የባሕር በር ይገባናል ጥያቄን ቁልፍ አጀንዳ አድርገን እየሠራን ነው ብለዋል። ነገር ግን ይህ ታላቅ ስኬት እና የሕዝብ ተነሳሽነት እረፍት የነሳቸው ታሪካዊ ጠላቶች ከውስጥ ባንዳዎች እና ጽንፈኞች ጋር አብረው ኀብረተሰቡን አውከዋል ነው ያሉት።
ለማኀበረሰቡ የሃይማኖት እና የብሔር አጀንዳ እየዘረጉ እረፍት በመንሳት የቆዩ ጽንፈኞች የሀገሪቱን ማነስ ከሚሹ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር አብረው በአማራ ሕዝብ ላይ ግፍ እየፈፀሙ መኾናቸውንም ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው አብራርተዋል። የደሴ ከተማ ሕዝብ ከመሪዎቹ ጎን በመሠለፍ እና የሰላሙ ዘብ በመኾን ሀገር ለማፍረስ በጉያው የሚንቀሳቀሱ ተላላኪዎችን ያለ ምህረት መታገል ይገባልም ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!