
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ አምስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰኔ 04/2012 ዓ.ም ባካሄደው 16ኛ መደበኛ ስብሰባው በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ሲመክር ውሎ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡
የምክር ቤቱ የሕግ፣ ፍትሕና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤትን ሕጋዊ ሰውነት ለመስጠት የቀረበ ረቂቅ አዋጅ በተመለከተ ያቀረበውን ሪፖርትና የውሳኔ ሐሳብ መርምሮ አዋጁን በአንድ ተቃውሞ እና በአብላጫ ድምጽ አጽድቆታል፡፡ ይህን ተከትሎ የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ለሙስሊም ማኅበረሰብ የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት አስተላልፏል፡፡
ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ ሰኢድ መሐመድ የምክር ቤቱ ሕጋዊነት የቀድሞ የመጅሊስ መሥራች አባቶች የበርካታ ዓመታት ትግላቸው ፍሬ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በዚህም ለሕዝበ ሙስሊሙ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡
“በታሪካዊ አመሠራርቱ እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት የቀደምት መሻኢኾች የሙስሊሙን ኅብረተሰብ መብት ለማስከበር ባደረጉት ጥረት እና በከፈሉት መሥዋዕትነት ከ45 ዓመታት በፊት የተመሠረተ ተቋም ነው” ብለዋል ሼህ ሰኢድ መሐመድ በመግለጫቸው፡፡
ይሁን እንጂ የመጅሊሱ ሕጋዊነት ባለፉት 45 ዓመታት በየአምስት ዓመቱ በሚታደስ የምስክር ወረቀት ላይ የተመሠረተ እንደነበር ጠቁመዋል፤ በቋሚነት በአዋጅ ዕውቅና እንዲሰጠው ያላሰለሰ ትግል ላደረጉ እና ዛሬ ለደረሰበት ደረጃ እንዲደርስ ከፍተኛ መሥዋዕትነት ለከፈሉም ምሥጋና አቅርበዋል፡፡
“ከሁሉም በላይ የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን የዘመናት የመብት ጥያቄ በውሉ በማዳመጥ የሃይማኖት እኩልነት እንዲረጋገጠ እና ይህ አዋጅ እንዲጸድቅ በቁርጠኝነት አመራር ለሰጡት ለኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶክተር)፣ ፍትሐዊ ውሳኔ ላሳረፉት የሚኒስትሮች ምክር ቤት እና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ምሥጋና ይገባቸዋል” ብለዋል ፕሬዝዳንቱ፡፡
ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው