ዳውንሲንድረም የሕጻናት ሕመም ምንድን ነው?

5
ባሕርዳር፡ መስከረም 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕርዳር ፈለገሕይወት ሰፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሕጻናት ስፔሻሊስት ሐኪም አያል መኳንንት እንደገለጹት ዳውንሲንድረም ቀጥታ ሳይንሳዊ መጠሪያው ጥቅም ላይ ይውላል እንጅ እስካሁን የአማረኛ አቻ ትርጉም እንዳልተሰጠው ገልጸውልናል።
✍️ዳውንሲንድረም ምንድን ነው?
የሕጻናት ስፔሻሊስት ዶክተር አያል መኳንንት ዳውን ሲንድረም በተፈጥሮ ምክንያት የወንድ እና የሴት ዘር በሚገናኙ ጊዜ በሚፈጠር ዘረመል (chromosom) መጨመር የሚመጣ መኾኑን ነግረውናል።
ጉዳዩን ሲያብራሩም ዳውንሲንድረም አንድ ሰው በተፈጥሮው ከእናቱ 23 እና ከአባቱ 23 በድምሩ 46 ዘረመል ይወስዳል፤ ስለዚህ 46 መኾን እያለበት ከዘረመሎች መካከል 21ኛው ዘረመል ላይ ሦሥት ሲኾን ድምሩ 47 በመኾኑ ምክንያት የሚመጣ ለየት ያለ ተፈጥሮ መኖር ማለት ነው ብለዋል።
ሌላው አጋላጭ ምክንያት የእናት ዕድሜ መጨመር ሊኾን እንደሚችል ገልጸዋል። ብዙ ጊዜ ከ35 ዓመት ዕድሜ በላይ ባሉ ሴቶች የሚወለዱ ልጆች ላይ የመከሰት ዕድሉ ከፍ ያለ እንደኾነም ጠቅሰዋል።
ቀደም ሲል ዳውን ሲንድረም ያለበት ልጅ የወለዱ እናቶች ተጋላጭነት ከፍ ያለ መኾኑንም ጠቅሰዋል። ከዚህ ውጭ በትክክል ዳውንሲንድረም በዚህ ነው የመጣ የሚለው ነገር እንደማይታወቅ ተናግረዋል።
✍️ የዳውንሲንድረም ምልክቶች
የሕጻናት ስፔሻሊስት ሐኪሙ እንደነገሩን ዳውን ሲንድረም ያለባቸው ልጆች ላይ ከሚታዩ ምልክቶች ውስጥ ፦
👉 የዕድገት መዘግየት
👉 ሲቀመጡ እና ሲያወሩ መዘግየት
👉 ቶሎ ቶሎ መታመም
👉 ጠፍጠፍ ያለ አፍንጫ መኖር
👉 ምላስ ማውጣት
👉 አገጭ ትንሽ መኾን
👉 ፀጉር ሉጫ መኾን
👉 የራስ ቅል ጠፍጣፋ መኾን
👉 አንገት አጭር መኾን
👉 ሰውነት ትንሽ ከፍ ያለ መኾን
👉ደረት ሰፋ ያለ መኾን
👉 ቁመት ማጠር
👉 አነስ ብሎ ጠፍጠፍ ያለ የእጅ መዳፍ እና አጫጭር እጣቶች ሊታዩ ይችላሉ ብለዋል።
ነገር ግን ይላሉ የሕጻናት ስፔሻሊስቱ በሕክምና እስካልተረጋገጠ ድረስ አብዛኛው ምልክቶች ቢታዩም ዳውን ሲንድረም አለ ብሎ መደምደም አይቻልም፤ ሌሎች ችግሮች ሊኾኑ ይችላሉ ነው ያሉን።
✍️ ዳውንሲንድረም እና ኦቲሲዝም አንድ ናቸው?
የሕጻናት ስፔሻሊስት ዶክተር አያል መኳንንት ዳውንሲንድረም እና ኦቲዝም እንደማይመሳሰሉ ተናግረዋል። ዳውንሲንድረም አለ ማለት ኦቲዝም አለ ማለት እንዳልኾነ ገልጸዋል። ነገር ግን ዳውንሲንድረም ያለባቸው ልጆች ላይ ኦቲዝም የመከሰት ዕድል ሊኖር እንደሚችልም ጠቅሰዋል።
✍️ዳወንሲንድረምን ለመለየት የሚደረጉ ምርመራዎች?
ዳውንሲንድረም ያለባቸው ልጆችን መለየት የሚቻለው በምርመራ ብቻ ነው ያሉት የሕጻናት ስፔሻሊስቱ የሚደረጉ ምርመራዎች በእርግዝና ወቅት እና ልጆች ከተወለዱ በኃላ በአራት አይነት መንገድ መኾኑን ነግረውናል።
በእርግዝና ጊዜ እንደ ሀገር ብዙ እየተሠራበት ነው ለማለት ባያስችልም ዳውንሲንድረም ያለባቸው ልጆች እንዳይወለዱ ማድረግ የሚያስችሉ ምርመራዎች ሊደረጉ እንደሚችሉ ጠቅሰዋል። ነገር ግን ውጤታማ ናቸው ለማለት እንደማያስችል ተናግረዋል።
የሕጻናት ስፔሻሊስቱ እንዳሉት ዳውንሲንድረምን ለመለየት በእርግዝና ጊዜ የአልትራሳውንድ እና ከእንሽርት ውኃ ተወስዶ የሚደረግ ምርመራ ይደረጋል ብለዋል።
ሕጻናት ከተወለዱ በኋላ ደግሞ በጤና ባለሙያዎች አማካኝነት ሕጻናቱ ላይ በሚደረግ ምልከታ ምልክቶችን በማየት ከ90 እስከ 95በመቶ በላይ መለየት ይቻላል ብለዋል።
በተጨማሪም የእናትነት እና የአባትነት ዘረመል ምልመላ እንዳለ ሁሉ የዳውን ሲንድረም ምርመራ ቀጥታ በመመርመር መለየት ይቻላል ነው ያሉት።
✍️ የዳውን ሲንድረም ተጓዳኝ የጤና ችግሮች?
ዳውን ሲንድረም ያለባቸው ልጆች ብዙ ተጓዳኝ የጤና ችግሮች ሊያጋጥማቸው ይችላል ይላሉ የሕጻናት ስፔሻሊስት ዶክተር አያል መኳንንት።
ከሚታዩ ችግሮች መካከልም፦
👉 በተለይ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበረሰባዊ ሥራዎች መሥራት ላይ የመሳተፍ ሙከራ ቢኖርም በትክክል መሥራት አለመቻል
👉ዐይናቸው በቀላሉ መታመም (የዐይን ሞራና ሌሎች ሕመሞች)
👉 አፍ አካባቢ ለመመገብ መቸገር
👉 በቀላሉ ለሳንባምች ሕመም መጠቃት
👉 የሆርሞን ችግር መኖር (በተለይ ለዕድገት ወሳኝ የኾነ የታይሮይድ ችግር)
👉የልብ ክፍተት ብዙ ጊዜ አብሮ መወለድ
👉 ለተከታታይ ባክቴሪያል ኢንፌክሽን መጋለጥ
👉አንዳንዴ አንጀት አካባቢ የአፈጣጠር ችግር መኖር
👉 የፊንጥጣ አፈጣጠር ችግር መኖር
👉 የደም ችግር መኖር
👉አንዳንዶች ላይ ደግሞ የስኳር በሽታ መከሰት
✍️ ዳወንሲንድረም እንዴት ይታከማል?
የሕጻናት ስፔሻሊስት ሐኪም አያል መኳንንት (ዶ.ር) ዳውንሲንድረም የዘረመል ችግር በመኾኑ በሕክምና ቴክኖሎጅ እስካሁን ዘረመልን የሚያክም ቴክኖሎጅ የለም ብለዋል። ሕክምና ማድረግ የሚቻለው ድጋፍ በመስጠት መኾኑንም ተናግረዋል።
ለበሽታ ተጋላጭ ስለኾኑም ሲታመሙ ማከም እና በቤተሰብ እየተደገፉ የተወሰኑ ሥራዎችን እንዲሠሩ ማድረግ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።
✍️ለዳውንሲንድረም ሕመም ተጠቂዎች የሚያስፈልግ እርዳታ
ዳውንሲንድረም ያለባቸው ልጆችን መንከባከብ ከሌላው ልጅ በተለየ ለአሳዳጊዎች ጫናው ጠንከር ያለ ነው ያሉት የሕጻን ስፔሻሊስት ዶክተር አያል መኳንንት የቤተሰብም ኾነ የሌሎች ሰዎች እገዛ ያስፈልጋቸዋልም ብለዋል።
መጀመሪያ ወላጆች ልጃቸው ዳውንሲንድረም እንዳለበት (እንዳለባት) እና የቤተሰብ እርግማን እንዳልኾነ የተፈጠረውን ነገር መቀበል እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
በተጨማሪም የንግግር፣ የሥራ እና የሌሎች ክህሎቶችን ማስተማር እና መደገፍ ያስፈልጋልም ብለዋል። ወደ ሃይማኖት ተቋማት እና ሌሎች ሰዎች ወደሚሠበሠቡባቸው አደባባዮች በመውሰድም አካባቢውን እንዲላመዱ ማድረግ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የዜጎችን ችግር የሚፈታ ነው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ
Next article“የቀይ ባሕር ባለቤቶች”