የመስቀል በዓል በመስቀለኛው ቦታ ይቋጫል።

16
ባሕር ዳር: መስከረም 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) መስቀል ለክርስትና ሃይማኖት ቤዛ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያኗ ጉልላት በምዕመኖቿ አንገት፤ በጳጳሳቶቿ አልባሳት በቀሳውስቶቿ ደረት፤ በመነኮሳቱ ቆብ በአማኒያኑ ልብ ሁሉ ሕያው ነው፡፡
መስቀል ለቤተ ክርስቲያኗ የንዋየ ቅድሳቶቿ ውበት፤ የበሮቿ ምልክት ተደርጎም ይወሰዳል፡፡ መስቀል ለክርስቲያኖች የድል ምልክት፤ የአሸናፊነት ትምህርት ነው፡፡ መስቀል በክርስቲያኖች ዘንድ የክርስቶስ ኢየሱስ ደም የፈሰሰበት፤ ፍቅሩ የተገለጠበት የድህነት ዓደባባይ ተደርጎም ይወሰዳል፡፡
የተበደለው ክሶ ለዳነችው ዓለም የሰው ልጅ ከፈጣሪው ጋር የታረቀው በመስቀል ነው ይላሉ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፡፡ ሰይጣን ከሰው ልጆች መንገድ ገለል የተደረገበት፤ የፈጣሪ እና ፍጡር መገናኛ ድልድይ ኾኖ ያገለገለው መስቀል ነው፡፡
በክርስቲያኖች ዘንድ መስቀል ለሰው ልጅ ዘላለማዊ ድኅነት ቤዛ ተደርጎም ይወሰዳል፡፡ ክርስቲያኖች የመስቀሉን ነገር አብዝተው ሲያስቡ ቅናት በጽናት ድል እንደኾነ፤ በደል በፍቅር እንደተሻረ ያንሰላስሉበታል፡፡ ከጥንት ጀምሮ የመስቀሉ ነገር ለተቸገሩት ክርስቲያኖች ረዳት፣ ለደከሙት አማኒያን ብርታት ኾኗቸዋልም፡፡ ንጹህ ሳለች በሴረኞች ሴራ ከትዳሯ በግፍ እንድትለያይ የተደረገችው ኢሌኒ ከተጣለችበት ባሕር እንዳለች በንጉስ እጅ ስር ወደቀች፡፡ በውበቷ ንጉሱን ያስደመመችው ሴት ታሪኳን ሲያዳምጥ ደግሞ በንጽሕናዋ ተማረከ፡፡ ያገባት፣ ሚስቱም ያደርጋት፣ ወደ ቤቱም ያስገባት ዘንድ ወደደ፡፡ “ሥራሽ ያውጣሽ” ተብላ ባሕር ላይ የተጣለችው ሴት ከንጉስ እጅ ላይ ወድቃ ንግሥት የመኾንን እጣ ፋንታ ታደለች፡፡
ንግስት ኢሌኒ ቆስጠንጢኖስም የተባለ ወንድ ልጅን ወለደች፤ ንጉስም ኾነ፡፡ ልጇ እንደልቧ መሻት ይሆንላትም ዘንድ ተሳለችለት፡፡ መሻቷ ሁሉ የኾነላት ሴት ክርስቶስ ኢየሱስ የተሰቀለበትን መስቀል ለመፈለግ ወደ ኢየሩሳሌም ሄደች፡፡ በብዙ ክፋት የተቀበረውን መስቀል በብዙ ልፋት ፈልጋ አገኘችው፡፡ ክርስቲያኖች ለመሰባሰባቸው ኅብረት፤ ለመዳናቸው ምክንያት የኾነው ቅዱስ መስቀል ክፉዎች ለብዙ ዘመን ከደበቁበት ተራራ በቅድስት ኢሌኒ እና በልጇ ቆስጠንጢኖስ ፍለጋ መገኘቱን መታሰቢያ በማድረግም የመስቀል በዓል በየዓመቱ መስከረም 17 ቀን በድምቀት ይከበራል፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ የመስቀል በዓልን በልዩ ሁኔታ ከሚያከብሩ ሀገራት መካከል አንዷ ናት፡፡ የክርስቶስ ኢየሱስ ግማደ መስቀል በመስቀለኛ ቦታ ዛሬም ድረስ ሕያው ኾኖ በግሸን ደብረ ከርቤ ይገኛልና፡፡
የአጼ ዳዊት መሻት እና ልፋት በልጃቸው አጼ ዘርዓይቆብ ተሳክቶ ግማደ መስቀሉ በመስቀለኛ ቦታ ላይ ያርፍ ዘንድ ተቻላቸው፡፡ የክርስቶስ ግማደ መስቀል ያረፈባት መስቀለኛዋ የግሸን አምባም ዳግማዊት ኢየሩሳሌም ትባል ዘንድ ተመረጠች፡፡ግሸን ደብረ ከርቤ በየዓመቱ መስከረም 21 ቀን ትነግሳለች፡፡ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የሃይማኖቱ ተከታዮችም በየዓመቱ ቀደም ብለው ወደ ግሸን ተራሮች ያቀናሉ፡፡ የበረቱት የመስቀል በዓልን በግሸን አምባ ላይ ያከብራሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ “የመስቀል በዓልም በመስቀለኛው ቦታ መስከረም 21 ቀን ይቋጫል”፡፡
ዘጋቢ:- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየአማራ ክልል መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ዛሬ ይጀምራል።
Next article“የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለመሻገር የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሠሩ ነው” ባንቺዓምላክ ገብረ ማርያም