
ደብረ ታቦር: መስከረም 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የመስቀል በዓል በደብረ ታቦር ከተማ በድምቀት ተከብሯል። በዓሉ የደቡብ ጎንደር ዞን ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብጹዕ አቡነ ሚካኤል፣ ሊቃውንት ቤተ ክርስቲያን፣ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች፣ የሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን እና ምዕመናን በተገኙበት በተለያዩ ሃይማኖታዊ ክዋኔዎች ነው የተከበረው።
የደቡብ ጎንደር ዞን ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብጹዕ አቡነ ሚካኤል “መስቀሉ ሲወጣ ሕሙማን የተፈወሱበት፣ ዐይነ ስውራንም ብርሃን ያዩበት ነው” ብለዋል።
በዓሉ ጥልን በመስቀሉ አሸንፎ፣ ተለያይተው የነበሩትንም አንድ ያደረገ ስለመኾኑም ነው ያስገነዘቡት።
“ምድሪቱ በእኛ ምክንያት አትረገም፣ ሰላም ካልኾነ መቀደስ እና ማስቀደስ፣ መዘመር እና ማወደስ አይቻልም፤ መስቀልም አይከበርም፤ እነዚህን ተግባራት ለማከናወን ምድሪቱ ከደም እርቃ ሰላም መኾን አለባት” ነው ያሉት።
“መስቀሉ የሚሰብከው እና የሚያስተምረን ሰላም ነው” ያሉት ብጹዕነታቸው “መልካም ትውልድ እንዲተካ፣ ትውልዱም መልካም ነገር እንዲያፈልቅ ታላላቆች ልጆችን መምከር እና መገሰጽ ይገባል” ብለዋል።
“ምድር ሲባረክ እና ሰማይና ምድር ሲስማሙ የሚበቅሉ አትክልቶች ሁሉ ለሰው ልጅ ተስማሚ ምግብ ይኾናሉ፤ ቅጠሉም ለፈውስ ይኾናል” ሲሉ ነው የሰላምን አስፈላጊነት ያብራሩት።
የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ኀይለ ኢየሱስ ሰለሞን መስቀል የመዳን፣ አንድ የመኾን እና ሰላምን የመሻት በዓል መኾኑን ተናግረዋል። “በመስቀሉ ሕይወትን የሰጠን የጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የፍቅር ማሳያ፣ የፍቅር በዓል ነውም” ብለዋል።
መስቀል የተጣሉትን የሚያስታርቅ፣ የተራራቁትን የሚያቀራርብ፣ ቂምና ቁርሾን ሽሮ አንድ የሚያድርግ ነው ያሉት አቶ ኀይለ ኢየሱስ በዓሉ የጥል ግድግዳ የፈረሰበት የሰላም ምልክት መኾኑን አክለዋል። በመኾኑም ከእርስ በእርስ ግጭት በመውጣት ሁሉም ሰላምን የሚያገኝበት እንዲኾን ተመኝተዋል።
መስቀል ሰላም፣ ፍቅር እና አንድነት ነው ያሉት ደግሞ ሀሳባቸውን ለአሚኮ ያካፈሉ የበዓሉ ታዳሚዎች ናቸው። በዓሉ ከሃይማኖታዊ ይዘቱ ባለፈ በማኅበራዊ ትስስር ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለውም ተናግረዋል።
መስቀል ጉርብትናን ከማጠናከር ባለፈ መስቀሉን ለማክበር የሚሰባሰቡት ሁሉ “የከርሞ ሰው ይበለን” በማለት እግዚአብሔርን ለቀጣይ ዓመት በሰላም እንዲያደርሳቸው የሚሳሉበት መኾኑን ተናግረዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!